ከቻይና የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ሪፖርት ጋር በተያያዘ “ከፍተኛ ጫና” እየተደረገብኝ ነው -የተመድ የሰብዓዊ መብት ኃላፊ
ተሰናባቿ ሚሼል ባችሌት “የስልጣን ዘመኔ ከማብቃቱ በፊት ሪፖርቱ ለመውጣት እቅድ አለኝ ” ብለዋል
ሚሼል ባችሌት፤ "በጫና ምክንያት የማወጣውም ሆነ የምተወው ሪፖርት የለም" ብለዋል
የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ፤ ከቻይናዋ ዢንጂያንግ ግዛት የመብት ረገጣ ሪፖርት ጋር በተያያዘ “ከፍተኛ ጫና” እየተደረገብኝ ነው አሉ፡፡
በመጪው ነሐሴ 31 ቀን 2022 የስልጣን ዘመናቸው የሚበቃው የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት በተቀሩት ሳምንታት ውስጥ፤ ቻይና ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ኡዩጉሁሮችን እና ሌሎች አናሳ ሙስሊም ወገኖችን በማሰር የተከሰሰችበትን በዚንጂያንግ ግዛት ስላለው የመብት ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ይፋ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ይታወቃል፡፡
ያም ሆኖ የስቃይ ማእከል እንደሆነች በሚነገርላት የዢንጂያንግ ግዛት ያለው የዜጎች ሰቆቃ የሚያጋልጥ ሪፖርት እንዲወጣ የሚፈልጉና የማይፈልጉ አካላት ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደሩባቸው እንደሚገኙ ባችሌት ተናግረዋል፡፡
"ሪፖርቱ ታትሞ እንዲወጣ የሚጠይቁ የደብዳቤዎችና ስብሰባዎች ብዛት መገመት አትችልም፤ በጣም ብዙ ነው፤ ላለፈው ዓመት ሙሉ በየቀኑ ፣ በእያንዳንዱ ጊዜ፣ በየስብሰባ ማለት ይቻላል" ሲሉም ነው የሚደርስባቸው ጫና ከፍተኛ መሆኑ ያስረዱት ኮሚሽነሯ፡፡
ከዚህም በተቃራኒ በደርዘን የሚቆጠሩ ሀገራት፤" ሪፖርቱ ታትሞ እንዳይወጣ የሚጠይቅ" ደብዳቤ ልከውልኛል ብለዋል ኮሚሽነሯ፡፡
ጥያቄዎቹ ማለቅያ የላቸውም በማለት በምሬት ሲናገሩም ተስተውለዋል በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሚገኙ በሚያሳብቅ መልኩ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡
በእንዲዘህ አይነት ጫና ውስጥ የገቡት ሚሼል ባችሌት ከባለፈው አመት ጀምሮ በተመድ መርማሪ ቡድን ሲጠና የቆየውና እየተንከባለለ የመጣው ሪፖርት በዚህ ጊዜ ይወጣል ለማለት “እርግጠኛ መሆን እንዳልቻሉም” ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመላክተው፡፡
ያም ሆኖ "ቃል የገባሁትን ለማድረግ በጣም ጠንክረን እየሞከርን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ይህ ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ እንደሚመጣ አውቅ ነበር ያሉት ባችሌት፤ "ነገር ግን በእንደዚህ አይነት ጫና ምክንያት የማወጣውም ሆነ የምተወው ሪፖርት የለም" ነው ያሉት ባችሌት፡፡
ቢሮዋቸው ከየትኛውም ሀገር ጋር በማንኛውም ጊዜ እንደሚያደረግው ነገሮች በጥንቃቄ ለመገምገም ጠቃሚ ነው ያላቸው ግበአቶች ከመንግስት (ከቻይና) ተቀብሏል ያሉት ባችሌት፤ "በሪፖርቱ ላይ እየሰራን ነው፤ የስልጣን ዘመኔ ከማብቃቱ በፊት ሪፖርቱ እንዲወጣ እቅድ አለኝ" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ባችሌት ከሁለት ወራት በፊት በቻይና ምዕራባዊው ከፍል በምትገኘውና የበርካቶች ማጎርያና የሲቃይ ማእከል እንደሆነች በሚነገርላት የዢንጂያንግ ግዛት የስድስት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
የባችሌት ጉብኝት አንድ የተመድ ከፍተኛ የስብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ቻይና ሲጎበኙ ከ17 ዓመታት በኋላ የተደረገ የመጀመርያው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ያም ሆኖ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ምዕራባውያን ሀገራት የባችሌት ጉዞ በቻይና የመብት ጭላንጭል እንዳለ ማሳያ አድርጋ ለማስረጃነት ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ነገር በወቅቱ አስጨንቋቸው እንደነበር ይታወሳል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ "በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ መጎብኘት ስህተት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች ዋና ዳይሬክተር ኬኔት ሮትም እንዲሁ የኮሚሸነሯ የቻይና ጉብኝት “ያልታሰበ አደጋ” ሲሉ ነበር የጠሩት።