የተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር በባንግላዲሽ የሚገኙ “የሮሂንጊያን መጠለያ ጣቢያዎች” ሊጎበኙ ነው
በመጠለያ ጣቢያዎቹ ወደ “አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የሮሂንጊያ ስደተኞች” እንደሚገኙ የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ
በያዝነው ወር መጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው የሚያበቃው ኮሚሸነር ባችሌት የባንግላዲሽ ጉብኝታቸው መጨረሻ መሆኑ ነው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት በባንግላዲሽ የሚገኙ የሮሂንጊያን መጠለያ ጣቢያዎች ሊጎበኙ ነው።
ሚሼል ባችሌት ወደ ዳካ የሚያቀኑት የባንግላድሸ መንግስት ባደረገላቸው ግብዣ መሰረት መሆኑ የተመድ ሰብዓዊ መብት ቢሮ አስታውቋል።
ኮሚሽነሯ ከእሁድ እስከ እሮብ በዳካ በሚያደርጉት ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲና እና ከሌሎች ሚኒስትሮች ጋር የሚገናኙ ይሆናል።
የባችሌት ቢሮ ባወጣው መግለጫ "ከፍተኛ ኮሚሽነሯ ወደ ኮክስ ባዛር በመጓዝ ከምያንማር የመጡ የሮሂንጊያ ስደተኞች የሚገኙባቸውን መጠለያ ጣቢያዎች ይጎበኛሉ” ማለቱም ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በመጠለያ ጣቢያዎቹ ፤ የምያንማር ወታደራዊ ጥቃትን ሸሽተው የመጡ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የሮሂንጊያ ስደተኞች እንደሚገኙ የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የምያንማር ጦር በፈረንጆቹ 2017 የመፈንቅለ መንግስት ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረበት አንስቶ በትረ ስልጣኑ አስካደላደለበት 2021 ድረስ በነበሩ ዓመታት ብቻ፤ 730 ሺህ የሮሂንጊያ ሙስሊሞች ወደ ባንግላድሽ መሰደዳቸው፣ በርካቶች በጅምላ መገደላቻው እና መደፈራቸው ሲዘገብ እንደበረም ይታወሳል።
ከአቅም በላይ ስደተኛችን ያስተናገደቸው ባንግላዲሽ፤ የተሸከመችውን ሃላፊነት ዓለም እንዳልተረዳላትና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዳላደረገላት በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ ትደመጣለች።
እናም ይህ የባችሌት ጉብኝት፤ ባንግለዲሽ የተሸከመቸውን ኃላፊነት የተቀረው ዓለም እንዲረዳው በማድረግ በኩል የራሱ የሆነ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የባችሌት ጉዞ በባንግላዲሽ የሚሰተዋሉትን የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ለማስቆም የሚያስችል ማስጠንቀቅያ የሚሰጡበት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆንም በመነገር ላይ ነው።
ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ 9 የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ ባቼሌት "ከህግ-ወጥ ግድያ፣ ማሰቃየት እና መጥፋትን ጨምሮ ከባድ የመብት ጥሰቶችን በአፋጣኝ እንዲቆም በአደባባይ መናገር አለባቸው"ብለዋል።
ባቼሌት ከባንግላዲሽ ከብሔራዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰዎች ጋር እንደሚገናኙም ተገልጿል።
በያዝነው ወር መጨረሻ የመጀመሪያው አራት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው የሚያበቃው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ባችሌት ሁለተኛ የስልጣን ዘመን እንደማይፈልጉ ከሁለት ወራት በፊት ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
እናም ይህ የባንግላዲሽ ጉብኝታቸው በተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነርነት የሚያደርጉት የመጨረሻ ጉብኝታቸው መሆኑ ነው።