ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንድትጀምር የአውሮፓ ህብረት አሳሰበ
ተወካዩ የኢሰመኮ እና የተመድን የጋራ የምርመራ ሪፖርት የአውሮፓ ህብረት እንደሚቀበለው ተናግረዋል
የአውሮፓ ህብረት ልዩ የሰብዓዊ መብት ተወካይ ኢሞን ጊልሞር በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ጉብኝት አድርገዋል
ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንድትጀምር የአውሮፓ ህብረት አሳሰበ፡፡
በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ጉብኝት አድርገው ወደ ብራስልስ የተመለሱት የህብረቱ ልዩ የሰብዓዊ መብት ልዩ ተወካይ ኢሞን ጊልሞር ጉብኝታቸውን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኢሞን ጊልሞር የህብረቱ የኮሎምቢያ ልዩ የሰላም ተወካይም ነበሩ፡፡
በመግለጫው በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እና ሌሎች የፌደራል ተቋማት መሪዎች ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ሆነው ያጠኑት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምርመራ ጉዳይ፣ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና የሰብዓዊ መብት ድጋፎች፤ በሶስት ቀናት የአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የመከሩባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች ናቸው እንደ ጊልሞር ገለጻ፡፡
ተወካዩ ኢሰመኮ እና የተመድ ሰብዓዊ መብት ባሳለፍነው ዓመት ይፋ ያደረጉት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የጋራ ምርመራ ሪፖርትን የአውሮፓ ህብረት እንደሚቀበለው ተናግረዋል፡፡
ይሁንና የጋራ ምርመራ ሪፖርቱ ግኝቶች ወደ ተግባር አልተቀየሩም፣ አጥፊዎችም ወደ ተጠያቂነት አልመጡም የሚሉት ልዩ ተወካዩ በዚህ ምርመራ መሰረት ዜጎችን በግፍ የገደሉ፣ አስገድደው የደፈሩ፣ የህግ ስልጣን ካለው አካል ውጪ ሰዎችን የሰወሩ እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሁሉ ሊጠየቁ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በግጭቶች እና በድርቅ ምክንያት 13 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአውሮፓ ህብረት መረጃ አለው ያሉት ጊልሞር ህብረቱ በተለይም በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በሶማሊያ ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ግጭቶችን በማቆም ለተጎጂዎች የሰብዓዊ መብት ድጋፍ ያለምንም ገደብ እንዲደርስ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉም አክለዋል ልዩ ተወካዩ፡፡
ኢሰመኮ ባሳለፍነው ሳምንት በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ያለው መካረር እየጨመረ መምጣቱን ገልጾ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት እንዳይነሳ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ተጽዕኖ እንዲያደርጉ አሳስቦ ነበር፡፡
ጊልሞር በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት እንዳይነሳ ህብረቱ ምን ሊያበረክት ይችላል? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም "በጦርነት የሚፈታ ችግር የለም፣ ተጨማሪ ዜጎች ለሞት እና ጉስቁልና ሊዳረጉ አይገባም ሁሉም አካላት ችግሮቻቸውን በውይይት ሊፈቱ ይገባል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል በኮሎምቢያ ከፋርክ አማጽያን ጋር የተደረሰውን ስምምነት እንደማሳያ በማንሳት፡፡
በሂደት ላይ ያለው ሃገራዊ የምክክር መድረክ 27ቱም የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በበጎ እንደሚያዩት የተናገሩት ልዩ ተወካዩ በዚህ መድረክ ላይ ሴቶች እና ወጣቶችን ማሳተፍ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጊልሞር በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከህወሓት ባለስልጣናት ወይ ተወካዮቻቸው ጋር ተገናኝተው እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ የፌዴራል መንግስቱን እንጂ የህወሓት ባለስልጣናትን ሊያገኙ እንዳልመጡ በመጠቆም አላገኘሁም ሲሉ መልሰዋል፡፡