ቻይና የአሜሪካ የመንግስት ተቋማት የኢሜል አድራሻዎችን በመበርበር ተወቀሰች
ማይክሮሶፍት 25 የአሜሪካ ተቋማት የኢሜል አድራሻዎች በቻይና የመረጃ መንታፊዎች መበርበራቸውን ገልጿል
ቤጂንግ በበኩሏ “የአለማችን የመረጃ ስርቆት መሀንዲሷ አሜሪካ ናት” በሚል ውንጀላውን አጣጥላዋለች
በቻይና የሚገኙ የመረጃ መንታፊዎች 25 የሚጠጉ የአሜሪካ ተቋማትን የኢሜል አድራሻዎች መበርበራቸው ተነገረ።
ግዙፉ የሶፍትዌር ኩባንያ ማይክሮሶፍት የመረጃ ጠላፊ ቡድንኑ “ስቶርም - 0588” የሚል ስያሜ እንዳለው ገልጿል።
በምዕራብ አውሮፓ ተደጋጋሚ የመረጃ ምንተፋ ሙከራ ያደረገው ቡድን በአሜሪካም የመንግስት ተቋማት ላይ ኢላማ አድርጎ ሲሰራ መቆየቱንም ነው ያስታወሰው።
ኩባንያው “ስቶርም - 0588” የትኞቹ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ የመረጃ ምንተፋ እንዳደረገ ግን አላብራራም።
የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ ማይክሮሶፍት ስለመረጃ ምዝበራ ጥቃቱ መረጃ እንደሰጠው ገልጿል።
የንግድ ሚኒስትሯ ጂና ራይሞንዶ ኢሜላቸው በመረጃ መንታፊዎቹ ከተበረበሩ ሰዎች መካክል እንደሚገኙበትም ነው የተነገረው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም በመንታፊዎቹ ኢላማ ተደርጎ ጥቃት እንደደረሰበት ነው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ የሚገኙት።
በለንደን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ግን ውንጀላው ተራ ስም ማጥፋት ነው ብሎታል።
“የአለማችን የመረጃ ስርቆት መሃንዲሷ አሜሪካ ናት” በሚልም ወቀሳውን እንዳጣጣለው ሬውተርስ ዘግቧል።
ማይክሮሶፍት በበኩሉ በቻይና የሚገኘው “ስቶርም - 0588” ከግንቦት ወር ጀምሮ በአሜሪካ የመንግስት ተቋማት ኢሜሎች ላይ ብርበራ ሲያደርግ መቆየቱንና ተጠቂዎቹን እያነጋገረ መሆኑን አስታውቋል።
ቻይና በግንቦት ወርም በጉዋም በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ ላይ የሳይበር ጥቃት ፈጽማለች በሚል የቀረበባትን ወቀሳ ውድቅ ማድረጓ የሚታወስ ነው።