ማይክሮሶፍት የቻይናውን ቲክቶክ ለመግዛት ንግግር መጀመሩ ተነገረ
የአሜሪካ ኩባንያዎች ቲክቶክን ለመግዛት "የጨረታ ጦርነት" ሲያደርጉ ማየት እንደሚሹ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ገልጸዋል
ትራምፕ ቲክቶክ እንዲከፈት ቢያደርጉም ለአሜሪካውያን በፍጥነት እንዲሸጥ ጫና እያደረጉ ይገኛሉ
ማይክሮሶፍት የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ የሆነውን ቲክቶክ ለመግዛት ንግግር እያደረገ መሆኑን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።
በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች ቲክቶክን ለመግዛት ፍላጎት ማሳየታቸውንና ንግግር ከጀመሩት ውስጥም ማይክሮሶፍት እንደሚገኝበት ነው ትራምፕ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
ከ15 ሚሊየን በላይ የቲክቶክ ተከታይ ያላቸው ትራምፕ መተግበሪያውን ለመግዛት የሚደረገውን "የጨረታ ጦርነት" መመልከት እንደሚሹም አብራርተዋል።
በ2020 የባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነውን ቲክቶክ ለመዝጋት ጥረት ያደረጉት ትራምፕ በባይደን አስተዳደር ታግዶ አገልግሎት አቁሞ የነበረውን ቲክቶክ እንዲከፈት የሚያስችል የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል።
ትዕዛዙ በ75 ቀናት ውስጥ ባለፈው አመት በኮንግረንሱ የጸደቀው ህግ እና በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚ እንደማይሆን ቢያመላክትም ፕሬዝዳንቱ ቲክቶክ ለአሜሪካውያን እንዲሸጥ ጫናቸውን አበርትተዋል ነው የተባለው።
ቢቢሲ እንደዘገበው አሁን ቲክቶክን ለመግዛት ንግግር የጀመረው ማይክሮሶፍት በነሃሴ ወር 2020 ያለከባድ ጨረታ የቲክቶክ ባለቤት የመሆን እድሉ በሩ ድረስ መጥቶለት ነበር።
ባይትዳንስ ኩባንያ ማይክሮሶፍት እንዲገዛው የቀረበለትን ጥያቄ አለመቀበሉም "አስገራሚ ነገር" ነበር ይላሉ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ናትያ ናዴላ።
ቲክቶክ ከማይክሮሶፍት በመቀጠል የአሜሪካ ድርሻውን እንዲገዛው የመረጠው ኦራክልንም ቢሆንም ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀርተዋል።
ከ170 ሚሊየን በላይ አሜሪካውያን የሚጠቅሙት ቲክቶክ አሁን ላይ የአሜሪካ ኩባንያዎች ሊገዙት የሚቋምጡለት ሆኗል።
በ30 ቀናት ውስጥ የመተግበሪያው ቀጣይ እጣፈንታ እንደሚታወቅ የገለጹት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወጣት መራጮችን ያገኙበት ቲክቶክ እንዲዘጋ እንደማይፈልጉ ደጋግመው ተናግረዋል።
በትናንትናው እለት በፍሎሪዳ ባደረጉት ንግግርም "ቻይና በማትሳተፍበት ሁኔታ ሁሉንም ስራዎች (ቲክቶክ የፈጠራቸው) ማዳን ከቻልን ሽያጩ ይከናወናል፤ የሚሆነውን አብረን እናያለን" ብለዋል።
የቻይና የስለላ መሳሪያ ሆኗል በሚል የሚቀርቡበትን ወቀሳዎች የማይቀበለውና የአሜሪካ ድርሻውን እንደማይሸጥ ሲገልጽ የቆየው ቲክቶክ በመጨረሻም ሸብረክ ይላል ወይ የሚለው ተጠባቂ ነው።
የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤለን መስክ፣ ቢሊየነሩ ፍራንክ ማክኮርት እና ካናዳዊው ኬቪን ኦሌሪ ቲክቶክን ለመግዛት ጥያቄ ካቀረቡት ውስጥ ይገኙበታል።
ታዋቂው ዩቲዩበር ጂሚ ዶናልድሰን (ሚስተርቢስት)ም ቲክቶክን ለመግዛት እየተደረገ ያለውን ፉክክር መቀላቀሉን በኤክስ ገጹ ማጋራቱ ይታወሳል።