በፓኪስታን ከ400 በላይ ተጓዞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ ባቡር በታጣቂዎች መጠለፉ ተነገረ
ታጣቂዎቹ በባቡር መስመር ላይ በፈንጂ ጉዳት ካደረሱ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎች የሚገኙበትን ባቡር ተቆጣጥረዋል

ለጥቃቱ ሀላፊነት የወሰዱ ተገንጣይ ታጣቂዎች መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን በ48 ሰዓታት ውስጥ የማይለቅ ከሆነ ታጋቾችን መግደል እንደሚጀምሩ ዝተዋል
የፓኪስታን “ባሎቺስታን ነፃ አውጭ ጦር” ተገንጣይ ታጣቂዎች ከ400 በላይ ተጓዞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ ባቡር መጠለፉቸው ተነግሯል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ታጣቂዎቹ በርካታ መጠን ያለቸው ፈንጆችን ታጥቀው ተሳፋሪዎችን ከእነባቡሩ መጥለፋቸውን ተናግረዋል፡፡
የጃፋር ኤክስፕረስ ንብረት የሆነው የመንገደኞች ባቡር ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 425 ሰዎችን ጭኖ የ1600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከሚገኙት ከኩዌታ ወደ ፔሻዋር ከተማ ጉዞ ላይ እያለ ነው ጠለፋው ያጋጠመው፡፡
የመንግስት ባለስልጣናት 190 ሰዎች በጸጥታ ሀይሎች ጥረት መለቀቃቸውን ገልፀው 37 ሰዎች ቆስለው በህክምና ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው በደቡብ ምዕራብ ባሎቺስታን ግዛት ውስጥ በምትገኘው ቦላን ከተማ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ሲሆን ፤ ታጣቂዎቹ ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ የባቡሩን ሾፌር ጨምሮ 8 የጸጥታ አባላት በአጠቃላይ 10 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡
በተጨማሪም ከታጣቂዎች መካከል 30 የሚሆኑት መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል፡፡
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻህባዝ ሻሪፍ ጥቃቱን አውግዘው የጸጥታ ሀይሎች ጥቃቱን ለማክሸፍ ጥረታቸውን መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞህሲን ናኪቪ በበኩላቸው አጥቂዎቹን የፓኪስታን "ጠላቶች" ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን ታጣቂዎቹ ሀገሪቱን ለማተራመስ የጀመሩትን ሴራ ለማክሸፍ ቃል ገብተዋል።
ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው የፓኪስታን ባሎቺስታን ነፃ አውጭ ጦር የፖለቲካ እስረኞች እና የማህበረሰብ አንቂዎች በ48 ሰዓት ውስጥ የማይፈቱ ከሆነ ታጋቾቹን መግደል እንደሚጀምር ዝቷል።
መንግስት በአሁኑ ወቅት የቀሩትን ተሳፋሪዎች ለመታደግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ፣ ሄሊኮፕተሮች እና የልዩ ሃይል አባላትን ማሰማራቱን ስካይ ኒውስ አስነብቧል፡፡
ተገንጣይ ታጣቂ ቡድኑ ከፓኪስታን ለመነጠል ባለፉት አስርት አመታት በሽምቅ ሲዋጋ የቆየ በአሜሪካ እና ብሪታንያ በሽብርተኝነት የተፈረጀ ነው፡፡
ባለፉት አመታትም የበርካታ ሰዎችን ህይወት የነጠቁ ጥቃቶችን ሲያደርስ የቆየ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ በፖሊስ ጣቢያዎች፣ የባቡር መስመሮች እና አውራ ጎዳናዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃቶችን በመፈጸም ይታወቃል፡፡