የሁለቱ ሀይማኖት ተቋማት የጾም መባቻ መልዕክት
ከነገ በስቲያ የሚገባውን የአብይ ጾም እና ከሳምንት በኋላ የሚጀምረውን የረመዳን ጾም አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የእስልምና ሀይማኖት መሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል

ሀይማኖቶቹ ጾሞቹን የአንድነት መፍጠሪያ እና ወደ ፈጣሪ መመለሻ ይሆኑ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል
የሁለቱ ሀይማኖት ተቋማት የጾም መባቻ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በተከታታይ የሚገቡትን የሁለቱን ሀይማኖቶች አጽዋማት አስመልክተው በተናጠል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
እንኳን ለ2017 ጾመ ኢየሱስ (አብይ ጾም) በሳላም አደረሳችሁ በሚል መልዕክታቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ ጾም ሀጥያትን ማሸነፍያ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
ፓትርያርኩ በመግለጫቸው “ጾም የመንፈሳዊ ልዕልና ማግኛ ፣ የሰይጣንን ፈተና መሻገሪያ ነው፤ ሰውነታችን በመብልና በመጠጥ ሲደነድን መልካም ኅሊና በውስጣችን ዓቅም ያጥረዋል፤ በአንጻሩ ደግሞ ሰውነታችን ከመብልና ከመጠጥ ሲለይ መልካም ኅሊና፣ ቁጥብነት፣ ማስተዋልና ማመዛዘን በውስጣችን ትልቅ ጉልበት ያገኛሉ” ብለዋል፡፡
ጾም ከመልካም ኅሊና የሚመነጭ መልካም ስራ ማከናወንን ይጠይቃል ያለው መግለጫው፤ “ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና ለመገዛት፣ ከዚያም ከቃሉ በተነገረን መሠረት የተራቡትን ልንመግብ፣ የተራቆቱትን ልናለብስ፣ የተጣሉትን ልናስታርቅ፣ ፍትሕ ያጡትን ፍትሕ እንዲያገኙ ልናደርግ፣ ሰብአዊ ክብር እንዳይነካ ጦርነት፣ ጥላቻ፣ አደገኛ የቃላት ውርወራና መነቃቀፍ እንዲቀር ልናደርግ ይገባል” ሲል አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የጾሙን ወቅት ምዕመናን የተራበውን በመመገብ፣ የተራቆተውን በማልበስ እንዲያሳልፉት እንዲሁም መሪዎች ፍትሕንና እኩልነትን በማስፈን ከነገሮች ሁሉ በፊት ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ በመስጠት ጾሙን እንዲያልፍ ቅዱስ ፓትርያርኩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮቸ ጠቅላይ ምክር ቤት በበኩሉ የ1446ኛውን የረመዳን ወር በተመለከተ በሰጠው መግለጫ የታላቁ የረመዳን ፆምን በመደጋገፍና ለሰላም በጋራ በመስራት ልንፆመው ይገባል ብሏል፡፡
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼህ ኢብራሂም ቱፋ በመልዕክታቸው “የረመዳን ወር መተባበር የሚልቅበት፣ አብሮነት የሚጠነክርበት፣ ፍቅር መተዛዘን የሚጎላበት ወር በመሆኑ ያለው ለሌለው እንዲያካፍል፣ አደጋ ላይ የወደቁ ሰዎች እንዲረዱና ሁሉም ለሰላም እንዲሰራ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም “ወሩ የቁርአን ወር በመሆኑ ለቁርአን ያለንን ክብር ለመግለፅ የሚያግዝ ሀገር አቀፍ የቁርአን ውድድር ተዘጋጅቷል” ብለዋል።