
አውሮፓውያን ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር ተጋጭተው ከወጡ በኋላ ከጎናቸው መሆናቸውን በመግለጽ ድጋፋቸውን እያሳዩ ሲሆን ሩሲያ በአንጻሩ ዘለንስኪ "ተዋረዱ" ስትል ተሳልቃለች
ከትራምፕ ጋር የተጋጩት ዘለንስኪ በዩኬ ሞቅ ያለ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተገልጿል።
በኃይትሀውስ ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር የተጋጩት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ለንግግር ለንደን ሲደረሱ የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) መሪ ኬየር ስትራመር ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለፈው አርብ እለት በኃይትሀውስ ኦቫል ኦፊስ በተደረገው ስብስብ ትራምፕ ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያለችውን ዘመቻ ከጀመረች ከሶስት አመት በኋላ ለዩክሬን የሚያደርጉትን ስብሰባ አቋርጣለሁ ሲሉ ዝተዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በትናንትናው እለት ከትራምፕና ዘለንስኪ ያወሩ ሲሆን የአርብ እለቱን የኃይትሀውስ ግጭት ተከትሎ በሰጡት ቃለ ምልልስ መረጋጋት እንዲፈጠር ጥሪ አድርገዋል።
ዘለንስኪ ወደ ለንደን ያቀኑት በዛሬው እለት በሚካሄደው የዩክሬን የሰላም እቅድ ላይ ለመሳተፍ ሲሆን ከዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ስትራመር ጋር ዳውንኒንግ ስትሪት ቢሮ ንግግር ለማድረግ ሲደርሱ መርካታ ሰው ተገኝቶ ድጋፉን ገልጾላቸዋል።
"ከመንገድ የሆነ ድምጽ እንደሰማህ ተስፋ አደርጋለሁ። ያ አንተን ለመደገፍ የወጣ የዩኬ ህዝብ ድምጽ ነው... አንተን ለመደጠፍ ፍጽም ቁርጠኞች ነን" ሲሉ ስትራመር ለዘለንስኪ ነግረዋቸዋል።
ስትራመር ዘለንስኪ በመላው ዩኬ ሙሉ ድጋፍ እንዳላቸው ነግረዋቸዋል ተብሏል።
"እስከመጨረሻው ከአንተና ከዩክሬን ጎን እንቆማለን"ብለዋል ስትራመር።
ከውይይቱ በኋላ ዩኬ ከዩክሬን ጋር የ2.26 ቢሊዮን ዶላር ብድር ስምምነት ተፈራርማለች።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪም ከጠቅላይ ሚኒስትር ስትራመር ጋር የዩክሬንን አቋም በማጠናከርና በአስተማማኝ የደህንነት ዋስትና ጉዳይ "ጠቃሚና ሞቅ ያለ" ንግግር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ወደ ኋይትሀውስ ያቀኑት የብርቅዬ ማዕድናት ውል ላይ ለመፈራረም የነበረ ቢሆን ሁለቱ መሪዎች መጋጨታቸው ተከትሎ ሳይሳካ ቀርቷል።
ጦርነቱን ለማስቆም ጥረት እያደረጉ ያሉት ትራምፕ ከሩሲያ ንግግር መጀመራቸው አውሮፓውያንንና ዩክሬንን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል። ዩክሬን የደህንነት ዋስትና የማይሰጣት ከሆነ ከአሜሪካ ጋር የማድዕን ስምምነት እንደማታደርግ ስትልገልጽ ቆይታለች።
የኔቶ ኃላፊ ማርኩ ሩቴ አሜሪካ ለዩክሬን ያደረገችውንና እያደረገች ያለውን ድጋፍ በማስታወስ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያስተካክሉ እንደነገራቸው ገልጸዋል።
አውሮፓውያን ዘለንስኪ በኃይትሀውስ ከትራምፕ ጋር ተጋጭተው ከወጡ በኋላ ከጎናቸው መሆናቸውን በመግለጽ ድጋፋቸውን እያሳዩ ሲሆን ሩሲያ በአንጻሩ ዘለንስኪ "ተዋረዱ" ስትል ተሳልቃለች።