ከ65 በመቶ በላይ የኔቶ አባል ሀገራት የጦር መሳሪያ ክምችታቸው መመናመኑ ተገለጸ
የኔቶ አባል ሀገራት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርበው ጦርነት ሁሉን አይነት ድጋፍ እያቀረቡ ናቸው
ሀገራቱ የጦር መሳሪያ ክምችታቸው የተመናመነው ለዩክሬን በመስጠታቸው እንደሆነ ተገልጿል
ከ65 በመቶ በላይ የኔቶ አባል ሀገራት የጦር መሳሪያ ክምችታቸው መመናመኑ ተገለጸ፡፡
በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል በሚል የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዘጠኝ ወራት ያለፉት ሲሆን እስካሁን ጦርነቱ መልኩን እየቀያየረ እንደቀጠለ ነው፡፡
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም ሞስኮን ከዓለም ንግድ እና ዲፕሎማሲ ከማግለል ጀምሮ የተለያዩ ማዕቀቦች ቢጣሉም ከሁለቱ ሀገራት ጀርባ ያሉ ደጋፊ ሀገራት መኖራቸው ጦርነቱ መልኩን እየቀያየረ እንዲቀጥል በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን ጥቃት እንድትመክት በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት አስተባባሪነት የጦር መሳሪያ፣ የቀጥታ ገንዘብ፣ ወታደራዊ መረጃዎችን እና ሌሎች ድጋፎችን እያገኘች ትገኛለች፡፡
30 አባላት ያሉት የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን በቀጥታ የጦር መሳሪያ በመስጠት ላይ ሲሆኑ አሁን ላይ የጦር መሳሪያ ክምችታቸው መመናመኑን ኒዮር ታየምስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ከ30 የኔቶ አባል ሀገራት ውስጥ ከ20 በላይ ያህሉ የጦር መሳሪያ እጥረት እንደገጠማቸው ሲገለጽ በቀጣይ ለዩክሬን ድጋፍ ላያደርጉ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
በተለይም አነስተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው የኔቶ አባል ሀገራት አቅማቸውን አሟጠዋል የተባለ ሲሆን አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ጣልያን፣ ኔዘርላንድ እና ጀርመን ብቻ ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ሊረዱ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረበት ካሳለፍነው የካቲት ጀምሮ ዩክሬን ከምዕራባዊያን ሀገራት 40 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎችን በድጋፍ መልክ አግኝታለች፡፡
ከዚህ የ40 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ውስጥ ግመሹን አሜሪካ የሸፈነች ሲሆን ድጋፏን እንደምትቀጥል ያስታወቀች ሲሆን ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን የሚሰጥ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ጦርነቱን ከማራዘም ባለፈ መፍትሄ አያመጣም ብላለች፡፡
የዩክሬን ጎረቤት የሖነችው ሉቲንያ ከእንግዲህ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ለኬቭ እንደማትሰጥ የገለጸች ሲሆን ጀርመን እና ሌሎችም የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በቀጥታ ማድረግ በኔቶ እና ሩሲያ መካከል የቀጥታ ጦርነትን ሊቀሰቅስ እንደሚችል ስጋታቸውን በመናገር ላይ ናቸው፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የቱንም ያህል ጊዜ ቢፈጅ ዋሸንግተን ለዩክሬን እስከ መጨረሻው ድረስ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡