ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ጦርነት ልጆቻቸውን ያጡትን “የሩሲያ እናቶች ሀዘን እንጋራለን” አሉ
ፑቲን፤ በዩክሬን ላይ ለጀመሩት ወታደራዊ ዘመቻ ምንም አይነት ጸጸት እንደማይሰማቸው ተናግረዋል
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት 5 ሺህ 937 የሩስያ ወታደሮች መገደላቸው ተገልጿል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ እያስከተለ ያለ ጦርነት መሆኑ ይታወቃል፡፡
እንደ አሜሪካ አገላለጽ ከሆነም ሩስያ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ ከ1962ቱ የኩባ ሚሳኤል ቀውስ ወዲህ በሞስኮ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ትልቁን ውጥረት አስከትሏል።
በጦርነቱ ከ300 ሺህ የሚበልጡ ተጠባባቂ ኃይሎችን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሩስያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ዘምተዋል፡፡
ደም አፋሳሹ ጦርነት ከሁለቱም ወገን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ገድሏል ወይም አቁስሏል፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት 5 ሺህ 937 የሩስያ ወታደሮች መገደላቸውን በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
የሩሲያ መንግስት የደረሰበት ኪሳራ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ልጆቻቸውን ወደ ጦር ግንባር በላኩት የሩሲያ እናቶች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ መፈጠሩም ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም በዩክሬን ሲዋጉ የነበሩ ወታደሮችን እናቶችን አግኝተው ያናገሩት ፕሬዝዳንት ፑቲን እርሳቸውና መላው የሩስያ አመራሮች የሩሲያ እናቶች ሀዘን እንደሚጋሩ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
"እኔ በግሌ እና መላው የሀገሪቱ አመራር - የእናንተን ህመም እንደምንጋራ እንድታውቁ እፈልጋለሁ” ሲሉም ነው ፑቲን የሩሲያ እናቶችን በመወከል ለውይይት ከተቀመጡት እናቶች ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት፡፡
ፑቲን በስሜት ውስጥ ሆነው ባስተላለፉት መልእክት “የወንድ ልጅ ማጣትን የሚተካ ምንም ነገር እንደሌለ ተረድተናል-በተለይ ለእናት " ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ይሁን እንጅ ፑቲን በዩክሬን ላይ ለጀመሩት ወታደራዊ ዘመቻ ምንም አይነት ጸጸት እንደማይሰማቸው ተናግረዋል፡፡
የፑቲንን አስተያየት ያዳምጡት እናቶች በበኩላቸው ለፑቲን የተለያዩ ሃሳቦች ያነሱላቸው ቢሆንም በሀገሪቱ ቴሌቭዥን ሳይተላለፍ ቀርቷል፡፡
ዩክሬን እና ምዕራባውያን የፑቲን ዘመቻ እንደ ግዛት ማስፋፋት ወረራ ቆጥረው ቢያጣጥሉትም፤ ሩሲያ ያሰበቸውን ሳታሳካና የኔ ናቸው የምትላቸውን ግዛቶች ከመጠቅለል የሚያስቆማት አንዳች ኃይል እንደማይኖር በተደጋጋሚ ስትዝት ትደመጣለች፡፡
በጦርነቱ ያጋጠማት ኪሳራ ስትገልጽ የማትሰማው ዩክሬን በበኩሏ የመጨረሻውን የሩሲያ ወታደር ከግዛቷ እስኪወጣ ድረስ እንደምትዋጋ ተናግራለች።