የዓለማችን “አደገኛው” የተባለው የሩሲያው R-36M2 አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል
እስከ 14 የጦር አረሮችን የሚሸከመው ሚሳዔሉ በአንድ ጊዜ በርካታ የተለያዩ ኢላማዎችን ማጥቃት ይችላል
ምዕራባውያን ይህን የሩሲያ ሚሳዔል “ሰይጣኑ SS-18 ሞድ 5” ሲሉ ይጠሩታል
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የአሁኗ ሩሲያ በርካታ የተራቀቁ የጦር መሳሪያዎችን መፍጠር የቻለች ሲሆን፤ በእነዚህ የጦር መሳሪያዎችም በጦረ ሜዳዎች ላይ ተቀናቃኝ መሆን ችለዋል።
ሩሲያ ከምትታወቅባቸው የጦር መሳሪያዎቿ ውስጥም ከአጭር ርቀት እስከ አህጉር አቋራጭ የሆኑ የተለያዩ አይነት ሚሳዔሎች ተጠቃሽ ናቸው።
ከእነዚህም ውስጥ “የዓለማችን አደገኛው ሚሳዔል” የተባለው የሩሲያው “R-36M2” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል አንዱ እና ዋነኛው እንደሆነ በስፋት ይነገርለታል።
ምዕራባውያን ይህን የሩሲያ ሚሳዔል “ሰይጣኑ SS-18 ሞድ 5” ሲሉ የሚጠሩት ሲሆን፤ ባለው ግዝፈት እና በሚሸከማቸው የጦር አረሮች የተነሳም የዓለማችን “አደገኛው” የሚል መጠሪያን እንዲያገኝ አድርጎታል።
ሚሳዔሉ “MIRV” የተባለ ሜከላኒዝም የተገጠመለት ሲሆን፤ ይህም በአንድ ጊዜ የተለያዩ ኢላማዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጽም የሚያስችለው መሆኑ ታውቋል።
R-36M2 አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል በመጠኑ በጣም ግዙፍ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ በሁለት ረድፍ እስከ 14 የሚደርሱ የጦር መሳሪያ አረሮችን መታጠቅ የሚችል ነው።
ሚሳዔሉ የጠላት ጦር በቀላሉ እንዳይመክተው የሚያደርግ አዲስ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት መሆኑም ነው የተነገረው።
ሩሲያ R-36M2 አህጉር አቋራጭ ሚሳዔልን ከዩክሬን ጋር ጦርነት ከጀመረች በኋላ ይፋ ያደረገች ሲሆን፤ ለምን ይህንን ጊዜ መረጠች የሚለው ግን እስካሁን ምለሽ አላገኘም።
ሩሲያ ሳርማት (አውሬው 2) የሚል መጠሪያ የተሰጠው አህጉር ቋራጭ ባሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ መሞከሯም ይታወሳል።
በሙከራው ወቅት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ “ሩሲያን ለመፈታተን የሚፈልጉ ጠላቶቻችን ቆም ብለው ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ እናደርጋለን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
“ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል 15 የኒኩሌር አረሮችን የሚሸከም ሲሆን፤ እስከ 35 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት በመብረር ማጥቃት ይችላል።