ዋትስአፕን ያገዱ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ግብጽ፣ ኳታርና ዮርዳኖስን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የዋትስአፕ አጠቃቀም ላይ ገደብ ጥለዋል
የሜታ ኩባንያ ንብረት የሆነው ዋትስአፕ እገዳ በጣሉ ሀገራት በ10 ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ድረስ መተግበሪያውን እየተጠቀሙ ነው ብሏል
የደህንነት ስጋትን በምክንያት የሚያነሱ ሀገራት ዋትስአፕን ጥቅም ላይ እንዳይውል አግደዋል።
ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሶሪያ መተግበሪያው ጥቅም ላይ እንዳይውል ካገዱት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ቻይናም ባለፈው ወር ዋትስአፕን ያገዱ ሀገራትን ጎራ ተቀላቅላለች።
ኳታር፣ ግብጽ፣ ይርዳኖስ እና አረብ ኤምሬትስ የድምጽ ጥሪን ጨምሮ በዋትስአፕ አጠቃቀም ላይ ገደብ የጣሉ ሀገራት ናቸው።
የሜታ ንብረት የሆነው ዋትስአፕ በበርካታ ሀገራት ቢታገድም በ10 ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሀገራቱ መተግበሪያውን እየተጠቀሙ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል ሃላፊው ዊል ካትካርት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
የቪፒኤን መስፋፋትና የዋትስአፕ ፕሮክሲ አገልግሎት እገዳውን ተላልፈው ሚሊየኖች መተግበሪያውን እንዲጠቀሙ ማድረጉን ነው ሃላፊው የገለጹት።
ዋትስአፕ መልዕክቶች ከላኪው ወደ ተቀባዩ ያለማንም ጣልቃገብነት እንዲደርሱ የሚያደርግና ሚስጢራዊነትን ለመጠበቅ የሚያስችል አሰራር አለው።
ብሪታንያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ግን ፖሊስ የዋትስአፕ መልዕክቶችን እንዲያነብ ሊፈቀድ ይገባል እያሉ ነው።