የሀገራዊ ውይይት አዘጋጅ ማይንድ ኢትዮጵያ በቀጣዩ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ዙሪያ መምከር ጀምሯል
የዛሬው የውይይት መድረክ የቅድመ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ሲሆን አጀንዳውም ብሔራዊ የውይይት መድረኩ ምን ይመስላል፣ማን ማን ይሳተፋሉ፣ከውይይቱ ምን ይጠበቃል፣ ማን ያወያያል እና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነበር።
ይህ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ከአንድ ወር በኋላ ማለትም ከጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ ማይንድ ኢትዮጵያ ገልጿል።
ይሁንና ይህ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ መቼ ይጠናቀቃል? ለሚለው ጥያቄ የምክክር መድረኩ ሁኔታን ዛሬ ላይ መናገር ስለማይቻል የምክክሩን መጠናቀቂያ ጊዜውን አሁን ላይ መናገር እንደማይቻል ተገልጿል።
በዚህ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ላይ የሰላም ሚንስቴር መንግስትን ወክሎ የሚገኝ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ምሁራን ፣የብዙሀን መገናኛዎች እና ሌሎች አካላት በአገር አቀፉ የምክክር መድረኩ ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ በየጊዜው በተፈጠሩ የፖለቲካ አለመግባባቶች ምክንያት ችግሮች እየተፈጠሩ አገርን ሲያውኩ ይስየዋላል። በነዚህ ችግሮች ምክንያት ንጹሀን ዜጎች ህይወት እንዲያልፍ አድርጓል።
ስምንት አገር በቀል የግል እና የመንግስት ተቋማት በጋራ በመሆን ማይንድ ኢትዮጵያ የተሰኘ ተቋም መስርተዋል።
እነዚህ ተቋማት ኢትዮጵያ የገጠማትን አለመረጋጋት እንድትፈታ በዚህ ተቋም አማካኝነት ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን የተቋሙ አባላት ተናግረዋል።
ይህ በስምንት ተቋማት ጥምረት የተመሰረተው ማይንድ ኢትዮጵያ በዚህ አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ማን ማን ይሳተፍ፣ አጀንዳው ምን ምን ይሁን፣ መድረኩን ማን ይምራው፣ አላማው ምን ይሁን እና መሰል አጀንዳዎች ዙሪያ ሲዘጋጅ መክረሙን አስታውቋል።
ማይንድ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ጀስቲስ ፎር ኦል፣ የሰላም ሚንስቴር፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ፣የሀሳብ ማዕድ እና የኢትዮጵያ ውይይት ውጥን የተሰኙ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በጋራ የመሰረቱት ተቋም ነው።
ማይንድ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አገራት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉም ተብሏል።
ለአብነትም ጀርመን፣ሆላንድ፣ዴንማርክ፣ስዊዘርላንድ፣አየርላንድ፣ፊንላንድ፣የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ይጠቀሳሉ።
ይህ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ኢትዮጵያውያን ብቻ ተሰብስበው እና መክረው ለችግሮቻቸው መፍትሔ የሚሰጡበት እንደሆነም ተገልጿል።
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መስከረም 24 አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡