የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከ13 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 426 ሚሊየን ዶላር ያስፈልገኛል አለ
ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን የጠየቀው በመጪዎቹ 6 ወራት የአስቸኳይ ድጋፍ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት ነው
ድርጅቱ አሁን ላይ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ 7 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጿል
የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያን 426 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግለት ጠየቀ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ እያደረገ ስላለው የሰብአዊ ድጋፍ እና በቀጣይ ስራዎቹ ዙሪያ በድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚካኤል ዱንፎርድ መግለጫ መስጠታቸውን ድርጅቱ በድረገጽ አስታውቋል።
አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እርዳታዎችን በማከፋፈል ላይ መሆኑን ገልጿል።
እንደ ደርጅቱ ገለጻ ከሆነ በትግራይ፤ አፋር እና አማራ ክልሎች 7 ሚሊየን ዜጎች የረሀብ አደጋ እንዳያጋጥማቸው የአስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በትግራይ ክልል 5 ነጥብ 2 ሚሊየን እርዳታ ፈላጊ ዜጎች እንዳሉ ሆኖ አሁን ላይ በአፋር ክልል 530 ሺህ ዜጎች እንዲሁም በአማራ ክልል 250 ሺህ ዜጎች የአስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ድርጅቱ ገልጿል።
በትግራይ ክልል ያሉ ተረጂዎችን ለመድረስ ከአፋር ክልል መንግስት ጋር በመነጋገር የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች እየተጓጓዙ መሆኑንም የድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል።
በኢትዮጵያ ከጦርነቱ በተጨማሪ ድርቅ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ እና የኮሮና ቫይረስ የአስቸኳይ ድጋፍ የሚጠይቁ ዜጎችን ቁጥር እንዳሻቀበው ድርጅቱ በመግለጫው አክሏል።
በዚህም መሰረት አሁን ላይ በኢትዮጵያ 13 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች የአስቸኳይ ምግብ ድጋፍን እንደሚፈልጉ ድርጅቱ አስታውቋል።
በጦርነቱ እና የአገሪቱ አካባቢዎች ባሉ ምክንያቶች የተናቀሉ እና ለእርዳታ የተዳረጉ ዜጎችን ለመርዳት 426 ሚሊየን ዶላር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግለትም ድርጅቱ ጠይቋል።
- የእርዳታ ምግብ የጫኑ 500 ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረሳቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለፀ
- በትግራይ “እርዳታን በአየር የማዳረስ ተግባር” በቅርቡ የመጀመር ተስፋ እንዳለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመላከተ
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ትናንት በሰጡት መግለጫ የፌደራል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ 538 ተሽከርካሪዎች የሰብዓዊ እርዳታዎችን ይዘው ወደ ክልሉ ገብተዋል ብለዋል።
እንዲሁም የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ለ4 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች ለአንድ ወር የሚሆን የሰብዓዊ ድጋፍ አስቀምጦ መውጣቱንም ሚኒስትሯ መናገራቸው ይታወሳል።
ይሁንና ወደ ክልሉ ከተሰማሩ ተሽከርካሪዎች መካከል 72 በመቶ ያህሉ እርዳታዎቹን ካደረሱ በኋለ እስካሁን አለመመለሳቸውን እና ተሽከርካሪዎቹ አሁን ላይ ምን እያደረጉ እንደሆነ መረጃ እንደሌላቸውም ሚኒስትሯ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።