በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ
ዓለም ዓቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ በጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ ይችላል- ዶ/ር ኤርጎጌ
ዓለም ዓቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በኢትጵያ ለ29ኛ ጊዜ ዛሬ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ የአካል ጉዳትና የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከግለሰብና ህብረተሰብ ባለፈ የአንድ አገርና የዓለም ህዝብ ባጠቃላይም የመላው የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ጉዳይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ለ80 አካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ አካል በነጻ የሰራው በጎ ፈቃደኛ
ማንም ሰው አካል ጉዳተኛ ላለመሆን ምንም ዓይነት ዋስትና የለውም የሚባለውም አካል ጉዳተኛነት በማንኛውም ሁኔታ፣ ጊዜና ስፍራ እንዲሁም በማንኛውም ሰው ላይ ከጽንሰት እስከ ህልፈት ሊደርስ የሚችል አንዱ የህይወት አጋጣሚ በመሆኑ ነውም ብለዋል።
በዓለም ከ1 ቢሊየን በላይ እንዲሁም በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል መገመት እምብዛም አዳጋች አይሆንም ብለዋል።
ሚኒስትሯ አሁንም የተዛባ አመለካከት ባልተገራበትና ትክክለኛ ግንዛቤ ባልያዘበት፣ አድልኦና መገለል ባልተወገደበት እንዲሁም የመረጃ ተደራሽነትና ትኩረት ባልሰፈነበት ማህበራዊ አውድ ውስጥ አካል ጉዳተኞች ከድህነት አዙሪትና ከጎስቋላ አኗኗር ይወጣሉ ብሎ ማሰብ አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድም የአካል ጉዳተኞች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት መብት ተገቢው ክብር፣ እውቅና ዋጋ እንዲያገኝ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
“የተጠቃለል የአካል ጉዳተኞች ህግ” ማዕቀፍ በረቂቅ ደረጃ እንዲዘጋጅ ጥረት ሲደረግ መቆየቱ ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ ሰነዱ ሲጠናቀቅና ጸድቆ በስራ ላይ ሲውል በዘርፉ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ውጤት እንዲያመጣ የበኩሉን እገዛ እንደሚደረግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሓመድ በበኩላቸው፤ የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ የአካል ጉዳተኞችን መሪነት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ይቀጥላል ብለዋል።
ዓለም ዐቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ፤ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።