አዲሱ መንግስት “ሃገሪቱን ከውድቀት ለመታደግ በሚያስችል መልኩ በስምምነት” መዋቀሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ተናግረዋል
በሚኒስትር ደረጃ ያሉ የካቢኔ አባሎቻቸውን የበተኑት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ አዲስ ካቢኔ አዋቀሩ፡፡
ሃምዶክ ካቢኔው ባለፉት ሶስት ወራት በፓርቲዎች መካከል ሲደረግ በነበረው ምክክር እና ስምምነት ሃገሪቱን ከውድቀት ለመታደግ በሚያስችል መልኩ ወቅታዊ ቀጣናዊ ስጋቶችን ታሳቢ አድርጎ መዋቀሩን ገልጸዋል፡፡
ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ካቢኔው ሲዋቀር ሃገራዊ መልክ እንዲኖረው ሆኖ መዋቀሩን ነው ሃምዶክ የተናገሩት፡፡
በካቢኔው ለውጥን በማቀጣጠል ድርሻ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አካላት፣ ወታደራዊ ቡድኖች እና የሰላም አጋሮች ተካተዋል፡፡
ይህ ካቢኔውን በልዩነቶች እንዲፈተን ሊያደርግ ይችላል፡፡
ሆኖም ከችግሮች የጸዳና የተላቀቀ ህብረት ሊኖር አይችልምና ለሃገሪቱ ደህንነት የሚበጅ እውነተኛ ትብብር እንዲኖር እንሰራለን ሲሉ ቃል ገብተዋል ሃምዶክ፡፡
የሽግግር ጊዜውን በወጉ የሚመራ ህግ አውጪ ሸንጎን በቶሎ ለማዋቀር በፍጥነት ሊሰራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ሃገሪቱ ዜና አገልግሎት ዘገባ ከሆነ ሸንጎው እ.ኤ.አ እስከ መጪው የካቲት 25 እንዲዋቀር እቅድ ተይዞለታል፡፡