“ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም በሚል የተነዛው ወሬ ኢትዮጵያን ካለመረዳት የመጣ ተራ ጩኸት ነው” መከላከያ ሚኒስቴር
ሰራዊቱ ከፌደራል ፖሊስ እና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል
የመተከል ዞን ወደ ሰላም እንዲመለስ ሰራዊቱ በትጋት እየሰራ እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል
“ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም በሚል የተነዛው ወሬ ኢትዮጵያን ካለመረዳት የመጣ ተራ ጩኸት ነው” መከላከያ ሚኒስቴር
አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ የመንግስትን የ 2013 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለጋዜጠኞች በተናገሩበት መግለጫቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ማንኛውንም ተልዕኮ ለመፈፀም በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ቀንዓ ያደታ የሰራዊቱ ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ፣ ገለልተኛ ተቋም መፍጠር መቻሉንም አስታውቀዋል። ሰራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ህገ መንግስታዊ መርህን መሰረት በማድረግ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሎችን የፀጥታ ግንባታ በተመለከተ ደረጃ ለማዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩ መቆየታቸውን የገለጹት ዶ/ር ቀንዓ የክልሎች የፀጥታ ግንባታ ለብሔራዊ አንድነት አደጋ ካላመጣ እና ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ እገዛ የሚያደርግ ከሆነ ያን ያክል የጎላ ችግር እንደሌለውም ተናግረዋል፡፡
እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ ሰራዊቱ ከፌደራል ፖሊስ እና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት በኩል በመልካም ጎኑ መታየቱን ተናግረዋል፡፡
የቀጣናውን ሰላም በጋራ ለመጠበቅ እና ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበትም ወታደራዊ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በመተከል ዞን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማስቆምና አካባበውን ወደ ሰላማዊ አንቅስቃሴ ለመመለስ ሰራዊቱ በአካባቢው ከሚገኘው ኮማንድ ፖስት ጋር በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር በማድረግ የተጠረጠሩ አካላትም በቁጥጥር ስር ውለው ተጠያቂ እየተደረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ሰሞኑን በአካባቢው የተከሰተው ችግር ምንም እንኳን መነሻው ግለሰባዊ ጸብ ቢሆንም ሰራዊቱ ግን በዚህ ድርጊት የተሳተፉትን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እና አካባቢው ወደ ቀድሞ ሰላሙ አንዲመለስ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም በሚል ሲነዛ የነበረው ወሬ ኢትዮጵያን በትክክል ካለማወቅና ካለመረዳት የመጣ ተራ ጩኸት ነው” ያሉም ሲሆን ሰራዊቱ ሀገሪቱን ከማናቸውም የጥፋት ተልዕኮ ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡