13 ሆቴሎች ደግሞ ባለ ሁለት እና አንድ ኮኮብ ሆቴል ደረጃ ሲያገኙ አንድ ሆቴል ከደረጃ በታች መሆኑ ተገልጿል
የቱሪዝም ሚንስቴር የ31 ሆቴሎችን ኮኮብ ደረጃ ይፋ አደረገ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር በዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጥራት መመዘኛ መስፈርቶ መሰረት በየዓመቱ ለሆቴሎች ደረጃ ይሰጣል።
ሆቴሎች በሚያገኙት የጥራት መመዘኛ መስፈርት አማካኝነትም የኮኮብ ደረጃዎች እንደሚያገኙ ይታወቃል።
የቱሪዝም ሚኒስቴርም አስገዳጅ መስፈርት ላሟሉ 31 ሆቴሎች የኮኮብ ደረጃ ምደባ ውጤታቸውን በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
ሚኒስቴሩ በ2014 እና 2015 ዓ/ም ለ64 ሆቴሎች ምዘና አድርጎ እንደነበር አስታውቋል።
በመመዘኛዎቹ መሰረትም ከተመዘኑት ውስጥ ለ31 ሆቴሎች የኮኮብ ደረጃን ሰጥቷል።
ከተመዘኑት ሆቴሎች መካከልም ሰባቱ የ4 ኮኮብ ደረጃሲሰጣቸው ዘጠኝ ሆቴሎች ደግሞ የ3 ኮከብ ደረጃን አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር እንዳስታወቀው አምስት ሆቴሎች የ 2 ኮከብ እንዲሁም ስምንት ሆቴሎች ደግሞ ባለ 1 ኮኮብነት ደረጃን አግኝተዋል።
ሁለት ሆቴሎች ደግሞ የተቀመጡ የጥራት መመዘኛ መስፈርቶችን አላሟሉም በሚል ከደረጃ በታች በሚል መለየታቸውን ማህበሩ አስታውቋል።
በዛሬው ዕለት የኮኮብ ደረጃቸው ይፋ የተደረጉት ሆቴሎች በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ እና አዳማ ከተሞች የሚገኙ ሆቴሎች መሆናቸው ተገልጿል።
የቱሪዝም ሚንስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የደረጃ ምደባው ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ በቅርበት ካሉ ተፎካካሪ ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ሲሉ ተናግረዋል ።
ሆቴሎች የኮኮብ ደረጃቸውን ለመለየት የአገልግሎት ጥራት፣ ለድንገተኛ አደጋዎች ያለ ዝግጅት ፣ ቅንጡ አገልግሎቶች መኖር፣ ንጽህና፣ ለተገልጋዮች ያሉ አማራጮች እና ተያያዥ ጉዳዮች እንደ ዋነኛ መስፈርትነት የሚወሰዱ ሲሆን ሆቴሎቹ መስፈርቶቹን መነሻ በማድረግ በባለሙያ ከተገመገሙ በኋላ የሚሰጡ ናቸው