ኢትዮጵያ የማትሳተፍበት የዓለም ቁንጅና ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ይጀመራል
በውድድሩ ላይ የ86 ሀገራት ቆነጃጅት የዓለም ቆንጆ ለመባል ይወዳደራሉ
ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይ በታሪክ በሞዴል ዲና ፍቃዱ አንድ ጊዜ ብቻ ተሳትፋለች
ኢትዮጵያ የማትሳተፍበት የዓለም ቁንጅና ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ይጀመራል፡፡
በሰሜን አሜሪካዋ ኤል ሳልቫዶር መዲና ሳን ሳልቫዶር የፊታችን ቅዳሜ የዓለም ቁንጅና ውድድር እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
የ86 ሀገራት ቆነጃጅት የምድራችን ቆንጆ ለመባል በሚፋለሙበት በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ከተሳታፊ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የለችበትም፡፡
ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2004 እስከ 2017 ድረስ በዚህ ውድር ላይ የሚሳተፉ ቆነጃጅትን ስትመርጥ የቆየች ቢሆንም በውድድሩ ላይ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ተወክላለች፡፡
ዲና ፍቃዱ በፈረንጆቹ 2006 ላይ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ በተካሄደው የሚስ ዩንቨርስ 2006 ውድድር ላይ ኢትዮጵያን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወክላ የተሳተፈች ቢሆንም በምርጥ 20 ቆነጃጅት ውስጥ መካተት ችላም ነበር፡፡
ከዚህ ዓመት በኋላ እስከ 2017 ድረስ ኢትዮጵያን በሚስ ዩንቨርስ የቁንጅና ውድድር ላይ የሚወክሉ ቆነጃጅትን በየዓመቱ በውድድር ቢመረጡም ከዲና ፍቃዱ ውጪ ቀሪዎቹ በውድድሩ ላይ አልቀረቡም፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚስ ዩንቨርስ ውድድር ላይ ለመካፈል ባቀደችበት በፈረንጆቹ 2004 ላይ ፍሬህይወት አበበ መኩሪያ በአዲስ አበባ በተካሄደው የቆነጃጅት ውድድር ላይ በአንደኝነት የተመረጠች ቢሆንም በውድድሩ ላይ ሳትካፈል ቀርታለች፡፡
ከ2018 ጀምሮም እስከዘንድሮው 2023 ድረስ በተካሄደው የሚስ ዩንቨርስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን የሚወክል ቆንጆ መምረጥ ባለመቻሉ ምክንያት መሳተፍ አልተቻለም፡፡
በዓለማችን ዜጎቻቸው ቆንጆዎች የሆኑ ሀገራት የትኞቹ ናቸውʔ
በዘንድሮው ውድድር ላይ ከአፍሪካ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ዚምባብዌን ጨምሮ ሰባት ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን ከ66 ዓመት በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ ያገቡ እና የወለዱ ሴቶች በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ ሀገርን እና ተሳታፊዋን ቆንጆ ከማስተዋወቅ ባለፈ በምርጥ 10 ውስጥ መካተት መቻል ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡
የዘንድሮውን ሚስ ዩንቨርስ 2023 ውድድር አሸናፊ የ250 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት ከማስገኘቱ ባለፈ ውድ እና ቅንጡ አልባሳትን በነጻ የማግኘት፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት የማስታወቂያ እድል፣ ዝነኛ መሆን እና ሌሎች ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡
ውድድሩ በበርካታ ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ ለሀገር እና ለአሸናፊ ቆነጃጅት ገጽታ ግንባታንም ያስገኛል፡፡