ሟቹ የምርጫ አስፈጻሚ በናይሮቢ ባለ አንድ ምርጫ ጣቢያ ሀላፊ ነበሩ
ደብዛቸው ጠፍቶ የነበሩት የኬንያ ምርጫ አስፈጻሚ ህይወታቸው አልፎ መገኘቱ ተገለፀ።
ጎረቤት ሀገር ኬንያ ለአምስተኛ ጊዜ የተካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያካሄደች ሲሆን የምርጫውን ውጤት በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርጋለች።
በምርጫው የ50 ዓመቱ ዊሊያም ሩቶ ለአምስተኛ ጊዜ የጠወዳደሩት ራይላ ኦዲንጋን ያሸነፉ ሲሆን፤ የምርጫውን ውጤት መገለጽ ተከትሎ በኬንያ የጸጥታ ስጋት እንዳይከሰት ተሰግቷል።
ይህ በዚህ እንዳለም በሀገሪቱ መዲና ናይሮቢ ባለ አንድ ምርጫ ጣቢያ ሀላፊ የነበሩ ግለሰብ ደብዛቸው ጠፍቶ የነበረ ሲሆን ዘግይቶ በወጣ መረጃ ግለሰቡ ህይወቱ አልፎ ተገኝቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ካሳለፍነው ዓርብ እለት ጀምሮ ደብዛው እንደጠፋ የተገለጸው እና ዳንአቼል ምቦሉ የተሰኘው ይህ ግለሰብ በኬንያ እና ታንዛንያ ድንበር አካባቢ ባለ አንድ ጫካ ውስጥ ህይወቱ አልፎ መገኘቱን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።
የሟች እህቶች ወንድማቸው እንደጠፋባቸው መናገራቸውን ተከትሎ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ግልሰቡ ህይወቱ አልፎ መገኘቱ እና አስከሬኑ በሁለት እህቶቹ መረጋገጡን ዘገባው አክሏል።
ፖሊስ፤ ሟቹ ምርጫ አስፈጻሚ በአካሉ ላይ የተለያዩ የማሰቃየት ጥቃቶች እንደተፈጸሙበት ማረጋገጡንም ገልጿል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዊሊያም ሩቶ ተቀናቃኛቸውን ራይላ ኦዲንጋን በ50.49 በመቶ በሆነ ድምስ ማሸነፉቸውን የምርጫ ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል።
ዊሊያም ሩቶ የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢን በምርጫ ቀደም ብለው ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።
ዊሊያም ሩቶ ተቀናቀኛቸውን ራይላ ኦዲንጋን በጠባብ ውጤት ሲመሩ ቆይተዋል። በምርጫው 22 ሚሊዮን ኬንያውያን ተመዝግበው ነበር።
በኬንያ የተካሄደው ምርጫ በአብዛኛው መመዘኛ ጥሩ የሚባል መሆኑን የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የሆኑት የቀድሞ ኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መግለጻቸው ይታወሳል።