ከተሰጠውና እስካሁን ከተቆጠረው ድምፅ 52 በመቶ ያህሉን ማግኘታቸው ነው የተነገረው
በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እየመሩ ነው ተባለ።
ሩቶ በሳለፍነው ሳምንት ማክሰኛ ከተሰጠውና እስካሁን ከተቆጠረው ድምፅ 52 በመቶ ያህሉን ማግኘታቸውን የሐገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን የቆጠራ ውጤቶች አመልክተዋል።
ሮይተርስ ከ291ዱ ምርጫ ጣቢያዎች የ266ቱን ውጤት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሩቶ 52 በመቶውን ድምፅ ማግኘታቸውን ዘግቧል።
ዴይሊ ኔሽን ደግሞ የ253ቱን ጣቢያዎች ውጤት ታሳቢ በማድረግ ሩቶ 51 በመቶ አግኝተዋል ብሏል።
የሩቶ ፓርቲ ዩናይትድ ዲሞክራቲክ ፍሮንት (UDA) በሃገሪቱ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከተሰጠው ድምጽ አብላጫውን አግኝቶ ማሸነፉንም የሐገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል።
ምርጫውን የማሸነፉን ቅድመ ግምት አግኝተው የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ 48 በመቶ ያህል ድምፅ ማግኘታቸውን ደግሞ ሁሉም ዘግበዋል።
የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው አሸናፊ በ7 ቀናት ውስጥ እንዲገለፅ የሃገሪቱ የምርጫ ህግ ያስቀምጣል።
ይህንኑ ተከትሎ ምርጫ ኮሚሽኑ ዛሬ ወይ ነገ ውጤቱን ይፋ ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል።
ውጤቱን ተከትሎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሃገሪቱ የጸጥታ አካላት ተሰማርተዋል።