በዚምባቡዌ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ “አዞው” ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን አሸነፉ
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ኤመርሰን ምናንጋዋ 53 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ገልጿል
ተቃዋሚዎች እና አለማቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች በምርጫው ሂደትና ውጤት ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው
በዚህ ሳምንት በዚምባቡዌ በተካሄደው ምርጫ “አዞው” በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ኤመርሰን ምናንጋዋ ማሸነፋቸው ተነገረ።
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ምናንጋዋ 53 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ትናንት ምሽት ይፋ አድርጓል።
የኤመርሰን ምናንጋዋ ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበሩት የ”ሲቲዝን ኮሊሽን ፎር ቼንግ” ፓርቲ መሪው ኔልሰን ቻሚሳ በበኩላቸው 44 ከመቶ መራጭ ማግኘታቸውን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
ምናንጋዋ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን መመረጣቸው እንደማይቀር ሲገለጽ መቆየቱን የሚያወሳው ሬውተርስ፥ ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንቱ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ አልፈቀዱም ሲሉ ይወቅሷቸዋል ብሏል።
የዚምባቡዌ ምርጫ ኮሚሽን ትናንት የዛኑ ፒኤፍ ተወካዩ ምናንጋዋን ማሸነፍ እንዳበሰረም ተቀናቃኛቸው ኔልሰን ቻሚሳ የሚመሩት ፓርቲ ተቃውሞውን አሰምቷል።
“ምንም አይነት ማጣራት ያልተካሄደበትን እና በጥድፊያ የተካሄደ ድምጽ ቆጠራ ውጤትን አንቀበልም” ሲልም በኤክስ (ትዊተር ገጹ) ላይ አስፍሯል።
ፓርቲው በቀጣይ የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተም ማብራሪያ እንደሚሰጥ ነው ያስታወቀው።
የአለማቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችም ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ነው ለመባል የሚጎድሉት ነገሮች እንዳሉ አንስተዋል።
የአውሮፓ ህብረት እና የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ (ሳድክ) ታዛቢዎች ከምርጫው አስቀድሞ ተቃዋሚዎች የጠሯቸውን ሰልፎች መታገዳቸውና የተለያዩ ፓርቲ አመራሮች መታሰራቸውን ተናግረዋል።
በብሄራዊ ቴሊቪዥን ጣቢያዎች ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰጠው ጊዜም አድልኦ የታየበት ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ምናንጋዋ የሚመሩት ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ግን የሚነሱ ቅሬታዎችን በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርጋቸው ቆይቷል።
በ2017ቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የመጀመሪያውን የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ የተኩት ኤመርሰን ምናንጋዋ በ2018 በምርጫ አሸንፈው ስልጣናቸውን ማጽናታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ በምርጫው ዋዜማ የዚምባቡዌ ዜጎች ተስፋን የሚያለመልሙ ንግግሮችን ቢያደርጉም ሀገሪቱን በዋጋ ንረት ከአለም ቀዳሚ ከማድረግ ውጭ ህይወት የሚቀይር ስራ አልሰሩም በሚል ይወቀሳሉ።
የሃምሌ ወር የዋጋ ግሽበት 101 ነጥብብ 3 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ መደበኛ ስራ ያላቸው የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥርም 25 ከመቶ ብቻ ነው ተብሏል።