ሳላህና ክሎፕ የተጋጩበት ምክንያት ምንድን ነው?
ሊቨርፑል በለንደን ስታዲየም ከዌስትሃም ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ግብጻዊው አጥቂና ክሎፕ ቃላት ሲወራወሩ ታይተዋል
ሳላህ ዛሬ ስለጉዳዩ ማብራሪያ ከሰጠሁ “ነገሮች ይከራሉ” ብሏል
በ35ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሊቨርፑል በለንደን ስታዲየም ከዌስትሃም ጋር ነጥብ ተጋርቷል።
ቀያዮቹ 2 ለ 2 በሆነ ውጤት ጨዋታውን ማጠናቀቃቸው ከዋንጫ ፉክክር መውጣታቸውን ያረጋግጣል ተብሏል።
ሊቨርፑል ወሳኝ ነጥብ በጣለበት ጨዋታ የታየው የሞ ሳላህ እና የአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ግጭት የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል።
በረቡዕ የመርሲሳይድ ደርቢ ሲወቀስ በሰነበተው የቀያዮቹ ቋሚ ተሰላፊ ዝርዝር ውስጥ ያልገባው ሳላህ በዛሬው ጨዋታ ወደሜዳ የገባው በ78ኛው ደቂቃ ነበር።
ውጤቱ እንዲቀየር የጓጉ የመሰሉት ጀርመናዊው አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ዌስትሃም ለጎል የተቃረበ ሙከራ ካደረገ በኋላ ግብጻዊውን አጥቂ በቃላት ሸንቆጥ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ሳላህ ለአሰልጣኙ ብስጭትና ንግግር ምላሽ መስጠቱን ተከትሎም ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።
ጃኦ ጎሜዝና ዳርዊን ኑኔዝ ሳላህን ገፍትረው ግጭቱን ለማብረድ ሲሞክሩም ታይቷል።
ሳላህ ከክሎፕ ጋር ቃላት ያወራወራቸውን ጉዳይ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥ ከጋዜጠኞች የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል ወጥቷል።
ለዘ አትላንቲክ ድረገጽ የሚዘበው እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ጀምስ ፒርስ ለሳላህ ጥያቄ አቅርቦለት፥ “ዛሬ ስለጉዳዩ ብናገር ነገሮች ይከራሉ” የሚል ምላሽ መስጠቱን ከምስል ጋር አያይዞ አቅርቦታል።
የያዝነው የውድድር አመት ሲጠናቀቅ ከሊቨርፑል ጋር የሚለያዩት የርገን ክሎፕ በበኩላቸው፥ “ጉዳዩን በመልበሻ ክፍል ውስጥ ተነጋግረንበት ተቋጭቷል” በሚል ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የቀድሞው የሊቨርፑል ተከላካይና የአሁኑ የእግርኳስ ተንታኝ ጀሚ ካራገር “ክሎፕን ያላስደሰተው ሳላህ ወደሜዳ ለመግባት ጊዜ መውሰዱ” ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።
ሊቨርፑል ዛሬ ከዌስትሃም ጋር ነጥብ መጋራቱን ተከትሎ ነገ በሰሜን ለንደን ደርቢ ከቶትንሃም ጋር ከሚጫወተው አርሰናል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ ብሏል፤ መድፈኞቹ ነገ ካሸነፉ ልዩነቱ ወደ አምስት ያድጋል።