ጠ/ሚ ሞዲ በአቡዳቢ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባውን የሂንዱ ቤተመቅደስ መረቁ
በ11 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው የሂንዱ ቤተመቅደስ ከ200 በላይ ሀገር ዜጎች የሚኖሩባት ኤምሬትስ ለእምነቶች እኩልነት የሰጠችውን ስፍራ ያሳያል ተብሏል
በሀገሪቱ ከመስጂዶች ውጭ 76 ቤተ አምልኮዎች እንዳሉ ይነገራል
በአቡዳቢ የተገነባው የመጀመሪያው የሂንዱ ቤተመቅደስ በህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ተመርቋል።
ኤምሬትስ 11 ሄክታር መሬት ሰጥታ ነው የሂንዱ ቤተመቅደሱ የተሰራው።
ከ95 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ቤተመቅደሱ ኤምሬትስ ለሃይማኖቶች ነጻነትና መከባበር የሰጠችውን ትኩረት ያሳያል ተብሏል።
ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህንዳውያን የሚኖሩባት ኤምሬትስ እያንዳንዱ ነዋሪዋ የፈለገውን እምነት የመከተልና የማምለኪያ ስፍራ የማግኘት ሰብአዊ መብት እንዳለው ታምናለች።
የተለያየ ማንነትና እምነት ያላቸው ከ200 በላይ ሀገር ዜጎች የሚኖሩባት እንደመሆኗም ለማምለኪያ ስፍራዎች ግንባታ የሚሆን ሰፋፊ መሬት በነጻ በመስጠት ትታወቃለች።
በሀገሪቱ ከመስጂዶች ውጭ 76 ቤተ አምልኮዎች መኖራቸውም የዚህ ማሳያ ነው።
አረብ ኤምሬትስ የሁሉንም እምነቶች ነጻነት ማስጠበቅና መከባበር ለሰላምና እድገት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በማመንም በ2023 በፌደራል ህጓ አካታው ለእምነት ተቋማት ግንባታ ልዩ ቦታ ሰጥታለች።
በዛሬው እለት የተመረቀው የሂንዱ እምነት ቤተመቅደስም በኤምሬትስ የሚኖሩ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህንዳውያን እምነት ክብር የሰጠ ሆኗል።
የኤምሬትስ መስራችና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን በቫቲካን እና በአውሮፓ የተለያዩ የእምነት ተቋማት ያደረጉት ጉብኝት ሀገሪቱ ከምስረታዋ ጀምሮ ለሃይማኖት እኩልነትና መከባበር ያላትን ቀናኢነት የሚያሳይ ነው።
በ1965ም ሼክ ሻክቡት ቢን ሱልጣን አል ናህያን በነጻ በሰጡት መሬት የተገነባው የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን መመረቁ ይታወሳል።
ኤምሬትስ በኢራቅ ሞሱል ከተማ በጦርነት ምክንያት የፈራረሱ ቤተክርስቲያኖችን ዳግም ለማስገንባት ቀድማ ጥረት ያደረገችና የደገፈች ሀገር መሆኗም አይዘነጋም።
ባለፈው አመት የተመረቀውና የክርስትና፣ አይሁድ እና እስልምና አምልኮ ስፍራዎችን በአንድ ያቀፈው “ኢብራሂሚ ፋሚሊ ሃውስ”ም ኤምሬትስ ለነዋሪዎቿ እምነት መከበር የሰጠችውን ቦታ ያመላክታል።