ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ከ3 ሺህ በላይ ታንኮችን ማጣቷ ተነገረ
አለማቀፉ የስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም ባወጣው ሪፖርት ዩክሬንም ሁለት አመት ሊደፍን በተቃረበው ጦርነት ከፍተኛ ኪሳራ እንደገጠማት አመላክቷል
ሞስኮ አሁን ባላት የመሳሪያ ክምችት ለሶስት አመት ጦርነቱን ያለችግር ማስኬድ ትችላለች ብሏል ተቋሙ
ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ከ3 ሺህ በላይ ታንኮችን ማጣቷን አለማቀፉ የስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም ገለጸ።
ተቋሙ ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርት ሞስኮ በዩክሬን የወደሙባት ታንኮች ብዛት ከጦርነቱ በፊት ስራ ላይ ከነበሩት ጋር የሚስተካከል ነው ብሏል።
ሩሲያ ባለፈው አመት ብቻ 1 ሺህ 120 ታንኮቿን ብታጣም አሁንም ከዩክሬን ካላት በእጥፍ የሚልቅ ታንክ ባለቤት መሆኗንም ነው አለማቀፉ የስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም ያስታወቀው።
በቀን በሶስት ፈረቃ አገልግሎት ካቆሙ የቆዩ ታንኮችን በማደስ ላይ የምትገኘው ሞስኮ፥ በወር 90 ታንኮችን የመስራት አቅም እንዳላት የተቋሙ ከፍተኛ ባለሙያ ሄነሪ ቦይድ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
በዚህም ባለፈው አመት ብቻ ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 500 ታንኮችን ወደ አገልግሎት ማስገባቷን ይጠቅሳሉ።
አዳዲስ ታንኮችን በማምረት የተጠመደችው ሩሲያ አሁን ላይ ባላት የታንክ ክምችት ብቻ እስከ ሶስት አመት የከፋ ጉዳት ሳይደርስባት ጦርነቱን መመከት ትችላለችም ብለዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ግን በአለማቀፉ የስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ አስተያየቱን አልሰጠም።
ተቋሙ ከ11 ቀናት በኋላ ሁለት አመት በሚደፍነው ጦርነት ዩክሬንም በርካታ ታንኮቿን ማጣቷን ቢያመላክትም በአሃዝ አልጠቀሰም።
ኬቭ ከምዕራባውያን የምታገኘው ድጋፍ የገጠማትን ችግር በተወሰነ እንድታልፍ አግዟታል የሚለው ሪፖርቱ፥ ፈጣን ድጋፍ ካልተደረገላት የመልሶ ማጥቃት መጀመር እንደሚከብዳት አመላክቷል።
በሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከባድ ውጊያ እያስተናገደ የመሄዱ ጉዳይም አጠራጣሪ ነው ብሏል አለማቀፉ የስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም።