ሰሜን ኮሪያ የደቡብ ኮሪያውን ፕሬዝዳንት አማካሪ የኢሜል አድራሻ በመስበር በረበረች
ፒዮንግያንግ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በህዳር ወር ወደ ብሪታንያ ጉዞ ለማድረግ የያዙትን ቀጠሮና የተላላኳቸውን መልዕክቶችም መመንተፏ ተገልጿል
ሰሜን ኮሪያ ከ2016 ወዲህ የሳይበር ጥቃት በመፈጸም ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ማግኘቷ ይነገራል
ሰሜን ኮሪያ የደቡብ ኮሪያውን ፕሬዝዳንት አማካሪ የኢሜል አድራሻ ለመጥለፍ መሞከሯን ሴኡል አረጋግጣለች።
የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው የአማካሪው የኢሜል አድራሻ የተጠለፈው የግል ኢሜሉን ለመንግስት ስራ ማዋሉን ተከትሎ ነው።
የመረጃ ብርበራው የተፈጸመው ፕሬዝዳንቱ በህዳር ወር 2023 በብሪታንያ ጉዞ ለማድረግ ዝግጅት ላይ እያሉ ነበር ተብሏል።
ኩክሚን ኢቦ የተሰኘው የደቡብ ኮሪያ ጋዜጣ እንዳስበበው የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የልን የብሪታንያ የጉዞ መርሃግብር መመልከት ችለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የተላላኳቸው የኢሜል መልዕክቶችም መመንተፋቸውን ነው ጋዜጣው የዘገበው።
የፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጽህፈት ቤት ግን የኢሜል መልዕክቶቹ ስለመሰረቃቸው ማረጋገጫ አልሰጠም፤ የደህንነት ስርአቱ ከቁጥጥር ውጭ እንዳልወጣም ገልጿል።፡
የህዳር ወሩ የሳይበር ጥቃት ሰሜን ኮሪያ በደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት የቅርብ ሰዎች ላይ የፈጸመችው የመጀመሪያው የተሳካ የመረጃ ምንተፋ ነው ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ የሳይበር ጥቃት በማድረስ ሚስጢራዊ መረጃዎችን ብቻ አይደለም የምትመነትፈው፤ በኒዩክሌር ምክንያት የተዳከመውን ኢኮኖሚዋን ለመደገፍም የሰለጠኑ ባለሙያዎቿ ገንዘብ (በተለይ ክሪፕቶከረንሲ) በመዝረፍ ይታወቃሉ።
ሀገሪቱ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ 3 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በሳይበር ጥቃት አማካኝነት መዝረፏን የቢቢሲ ዘገባ ይገልጻል።
የመረጃ ምንተፋው የሀገራትን የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂዎች ኢላማ ያደረገ መሆኑም በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።