ፖላንድ ከህንድ ጋር በመከላከያ ኢንዱስትሪ ያላትን ትብብር ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች
የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ በፖላንድ ጉብኝት ላይ ይገኛሉ
ከ45 አመት በኋላ የህንድ መሪ ፖላንድን ሲጎበኝ ለመጀመርያ ጊዜ ነው
ፖላንድ ከህንድ ጋር በጦር መሳርያ ኢንዱስትሪ ያላትን ትብብር ማጠናከር እንደምትፈልግ አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶናልድ ተስክ በዋርሳው በጉብኝት ላይ ከሚገኙት የህንዱ አቻቸው ናሪንድራ ሞዲ ጋር በዛሬው እለት ተወያይተዋል፡፡
መሪዎቹ በሁለትዮሽ ኢኮኖሚዊ ፣ ፖለቲካዊ ግንኙነት እና በዩክሬን ሩስያ ጦርነት ዙርያ ትኩረት አድርገው ተነጋግረዋል፡፡
በዋናነት ከሩስያ የጦር መሳርያ አምራቾች በምትገዛቸው መሳርያዎች ጦሯን የምታስታጥቀው ፖላንድ የጦር መሳርያዎችን አይነት ለማብዛት እና አማራጭ ገበያ ለመፈለግ ከህንድ ጋር በቅርበት መስራት እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ የመከለከያ ጦራችንን የጦር መሳርያ አቅም እና ዘመናዊነት ለማሳደግ ከህንድ ጋር በጋራ መስራት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
በነገው አለት በዩክሬን ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት ጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ የሞስኮ እና ኬቭን ጦርነት ለማስቆም የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
አክለውም “አፋጣኝ ሰላምን ለማስፈን ዲፕሎማሲ እና ውይይት ቀዳሚው አማራጭ እንደሆነ አምናለሁ ይህም እንዲሳካ የምችለውን አደርጋለሁ” ነው ያሉት፡፡
በዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት ዙርያ መፍትሄ ለማፈላለግ ቀዳሚ አላማውን ያደረገ ጉብኝት በምስራቅ አውሮፓ እያደረጉ የሚገኙት የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር የኬቭ ዋነኛ ደጋፊ ከሆኑት ከፖላንድ አቻቸው ጋር በጉዳዩ ላይ ስለመምከራቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ስፍራው ከማቅናታቸው በፊት ሩስያ እና ዩክሬንን ለማቀራረብ ጥረት እንደሚያደርጉ መናገራቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ሀገራቱ መልዕክት እንዲለዋወጡ ፣ የግንኙነት መስመር እንዲኖራቸው እና ወደ መቀራረብ እንዲመጡ የራሳቸውን ሚና እንደሚወጡ ያስታወቁት ሞዲ ኬቭ እና ሞስኮን የማደራደር ሀላፊነት እንዲኖራቸው እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በነገው እለት ወደ ዩክሬን የሚያቀኑ ሲሆን በዚያም የቀጠናዊ እና የደህንነት ጉዳዮች ላይ ከፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዜለንስኪ ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሶቭየት ህብረት መፈራረስን ተከትሎ ዩክሬን እንደ ነጻ ሀገር ከተመሰረተች ከሶስት አስርት አመታት ወዲህ የህንድ ጠቅላይ ሚንስትር ዩክሬንን ሲጎበኝ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
በቅርቡ የሩስያ ምዕራባዊ ድንበርን ጥሶ በመግባት ድንገተኛ ጥቃት የፈጸመችው ዩክሬን ከሞስኮ ጋር ለድርድር ለመቀመጥ ጦሯን ከግዛቶቼ ታስወጣ በሚለው አቋሟ ጸንታለች፡፡