ከአስም በሽታ ለመፈወስ በህይወት ያሉ አሳዎችን የምታስውጠው የህንድ መንደር
ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ ነው በተባለው ባህላዊ ህክምና አሳን ከእነ ህይወቱ መዋጥ ለአስም ፍቱን መድሀኒት ነው ተብሎ ይታመናል
ታማሚዎች ወደ ጥንታዊታ መንደር በአመት አንድ ግዜ በማቅናት በህይወት ያሉ ትንንሽ አሳዎችን ይውጣሉ
በደቡባዊ ህንድ ሀይደርባድ በስነ ፈለክ የቀን አቆጣጠር በአመት አንድ ግዜ የሚሰጠው አሳን ከእነ ህይወቱ የመዋጥ ባህላዊ ልምድ ለአስም በሽታ ፍቱን ነው ተብሎ ይታመናል።
ከመላው ህንድ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የሚመጡ ህንዳዊያን ህክምናውን ለማግኝት ለሳምንት ወረፋ መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።
ቨርና ጎውድ የተባሉ የጥንታዊቷ ሀይደርባድ ከተማ ነዋሪ በ1845 “ከሰማይ አገኝሁት” ባሉት ፎርሙላ ተቀምሞ በሚዘጋጅ የእጽዋት ድብልቅ ውስጥ በሕይወት ያለውን ትንሽ አሳ ሰዎች እንዲውጡ የማድረግ ልምድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ነው።
ለ100 ዓመታት ሲተላለፍ የመጣው ልማድ ባትሀኒ በተሰኙት ቤተሰቦች ያለ ክፍያ በነጻ የሚሰጥ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ከአስም እና ከመተንፈሻ አካላት ጋር በተገናኝ ህመም ያለባቸው ህንዳዊያን ወደዚህ ስፍራ ይጎርፋሉ።
የህንድ የጤና ባለስልጣናት ህክምናው ምንም አይነት ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የሌለው ሌሎች የተወሳሰቡ የጤና እክሎችን ሊፈጥር እንደሚችልም በተደጋጋሚ ቢያስጠነቅቁም ልማዱን መስቆም አልቻሉም።
ህክምናውን ያስጀመሩት የቨርና ጎድ 5ተኛ ትውልድ የሆነው ካካርና አልካናንዳ እንደተናገረው “በህይወት ያለው አሳ ከሚቀመመው መድሀኒት ጋር ሲወሰድ በጉሮሮ ውስጥ ያለውን መጨናነቅ በማቃለል ሰዎች መተንፈሰ እንዲችሉ ያደርገቸዋል ፣ ህክመናውን ገንዘብ ለማግኝት አስብን የምናደርገው ሳይሆን ሰዎችን ከህመም ለማላቀቅ በነጻ የምንሰጠው ነው” ብሏል።
ከህንድ ዋና ከተማ ኒው ደልሂ 20 ሰአታት የባቡር ጉዞን አድርጋ የመጣችው አሽ ሞሀመድ “እናቷ ህክምናውን ለ7 አመታት እየተከታተለች እንደምትገኝ ገልጻ በዘመናዊ ህክምና በእናቷ ላይ ያላየችውን የጤና መሻሻል እንደተመለከተች” ገልጻለች፡፡
“ፕራስዳም” ወይም “ስጦታ” በመባል የሚጠራው ባህላዊ ህክምና በነጻ የሚሰጥ ሲሆን ታካሚዎች በአቅራቢያቸው ከሚገኝ የአሳ መሸጫ በህይወት ያለ ትንሽ አሳ በ50 ሩፒ በመግዛት ብቻ ህክምናውን ያገኛሉ፡፡
የከተማዋ የጤና ባለስልጣናት ሂደቱ ከአጉል እምነት ጋር የሚገናኝ ነው በሚል እንዲቆም የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ ቢገኝም አሁንም ግን በሺዎች የሚቆጠሩ የአስም እና የመተንፈሻ አካላት ታማሚዎች በህይወት ያለ አሳ ለመዋጥ ወደ ህንዷ ሀይደርባድ ከተማ መጉረፋቸውን ቀጥለዋል፡፡