በሶማሊያ ሞቃዲሾ በደረሰ የሽብር ጥቃት በትንሹ የ100 ሰዎች ህይወት አለፈ
300 ሰዎች በጥቃቱ የቆሰሉ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ተሰግቷል
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጥቃቱን አልሻባብ እንዳደረሰው ገልጸው ሽብር ቡድኑን ለማጥፋት የተጀመረው ጥረት ይቀጥላል ብለዋል
በሶማሊያ ሞቃዲሾ በደረሰ የሽብር ድርጊት በትንሹ የ100 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ አልሻባብ የተሰኘው የሽብር ቡድን ባደረሰው የአጥፍቶ መጥፋት አደጋ ቢያንስ 100 ዜጎች መገደላቸውን ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ተናግረዋል፡፡
ጫካኔ የተሞላበት ይህ የሽብር ድርጊት 300 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል፡፡
“ህጻናት በእናቶቻቸው እና አባቶቻቸው እጆች ላይ እያሉ በጭካኔ ተገድለዋል ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ የሶማሊያ ህዝብ እና መንግስት አልሻባብን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የጀመሩትን ጥረት ይቀጥላሉም ብለዋል፡፡
የሶማሊያ ፖሊስ በበኩሉ በጥቃቱ ህጻናት፣ ሴቶች እና አዛውንቶች የአደጋው ሰላባ መሆናቸውን ገልጸው የሶማሊያ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ መሀመድ ኢሴ ከተገደሉት ውስጥ አንዱ መሆኑን ለሮይተርስ ተናግሯል፡፡
አልሻባብ በሁለት ቦታዎች በተሸከርካሪ ላይ የተጠመደ ቦምብ ባደረሰው የሽብር ጥቃት ህዝብ የሚሰበሰብባቸውን ቦታዎች ኢላማ እንዳደረገም ተጠቁሟል፡፡
አምቡላንስ የተጎዱ ሰዎችን በማንሳት ላይ እያለ በደረሰበት ሁለተኛው የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ከነአሽከርካሪው ወድሟል የተባለ ሲሆን የትምህር ሚኒስቴር ህንጻ እና በአካባቢው የገንዘብ ምንዛሬ የፈጽሙ የነበሩ ሰዎች በአደጋው መጎዳታቸው ተገልጿል፡፡
ሶማሊያ በአልሻባብ የሽብር ቡድን መጠቃት ከጀመረች 20 ዓመት ያለፋት ሲሆን ጠንካራ የፌደራል መንግስት ተመስርቶ ሰላማዊ ሶማሊያን ለመፍጠር የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም በአፍሪካ ህብረት ስር ላለው ሰላም አስከባሪ ሀይል ጦር ካዋጡ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን የሶማሊያ መንግስት በአልሻባብ ላይ የተጠናከረ ጥቃት ከከፈተ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ዓመራሮች በመያዝ እና በመገደል ላይ ሲሆኑ ቡድኑ በሶማሊያዊያን ላይ የሚያደርሰው የሽብር ጥቃት ግን እንደቀጠለ ነው፡፡