ሶማሊያ የአልሸባብ የቀድሞ ሁለተኛ ቁልፍ ሰውን በሚኒስትርነት ሾመች
የሶማሊያ መንግስት የአልሸባብ መስራች ሙክታር ሮቦ አሊን (አቡ መንሱር) ሚኒስትር አደርጎ ሾሟል
አቡ መንሱር የአልሸባብ የሽበር ቡድን መስራችና በምክትልነት የመራ ሰው ነበረ
አዲሱ የሶማሊያ መንግስት በርካቶችን ያስገረመ አዲስ ከቢኔ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ ቤሪ የተመራው አዲሱ የሶማሊያ መንግሰት የአልሸባብ የሽብር ቡድን ሁለተኛ ቁልፍ ሰውን በሚኒስትርነት በመሾሙ ነው በርካቶችን ያስገረመው።
በትናትናው እለት በሚቃዲሾ በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ልምድ እና ብቃት አላቸው ያላቸውን ሚኒስትሮቻቸውን አስተዋውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ "ሶማሊያውያን ከአለም ጋር ስምምነት ላይ ናቸው" በሚለው መርህ ላይ ለመስራት ቃል ገብተዋል።
ከዚህ ሁሉ ግን በርከቶችን ያስገረመው ጉዳይ በቅጽል ስሙ “አቡ መንሱር” በመባል የሚጠራው የአልሸባብ የሽብር ቡድን መስራች እና የቡድኑ ሁለተኛ ቁልፍ ሰው ሙክታር ሮቦ አሊ ሹመት ነበር።
ሙክታር ሮቦ አሊ (አቡ መንሱር) በአዲሱ የሶማሊየ መንግስት ካቢኔ ውስጥ የኃይማኖት ጉዳዮች እና የኢንዶውምንት ሚኒስትር ተደርገው መሾማቸውም ተነግሯል።
ሙክታር ሮቦ አሊ አልሸባብን ለቆ እስከወጣበት የፈረንጆቹ 2011 ድረስ የሽበር ቡድኑ ምክትል መሪ የነበረ ሲሆን፤ የሽብር ቡድኑ ይፋዊ ቃል አቀባይም ነበር።
በፈነረንጆቹ 2017 ላይ እጁን ለሶማሊያ መንግስት የሰጠው አቡ መንሱር፤ በወቅቱ በሰጠው መግለጫ ከቡድኑ ጋር የተለያየው ከ5 ዓመት በፊት እንደነበረ ገልጾ ነበር።
በፈረንጆቹ 2018 ላይ ደግሞ የደቡብ ምእራብ ሶማሊያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ተወዳድሮ እንደነበረም ይታወሳል።
አዲሱ ሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ ቤሪ በቴሌቭዥን በሰጡት አስተያየት፤ አልሸባብን ከመልቀቁ በፊት ለጠቆመው ሰው 5 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቶበት የነበረው ሰው አሁን ላይ የሶማሊያ ኃይማኖታዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኗል ብለዋል።