በሞቃዲሾ ከተቀሰቀሰው ግጭት ለመሸሽ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እየወጡ ነው
የሶማሊያ ፓርላማ የፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የስልጣ ዘመንን በ2 ዓመት ማራዘሙ ይታወሳል
በፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ደጋፊዎችና በተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይሎች መካከል ግጭት ተቀስቅሷል
የሶማሊያዋ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ነዋሪዎች በከተማዋ በመንግስት እና በተቃዋሚ ሀይሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት በመሸሽ ከተማዋን ለቀው እየወጡ ነው።
የከተማዋ ነዋሪዎች መጠነኛ መገልገያ ቁሳቁሶችን እየጫኑ መኖሪያ ቤታቸውን በመልቀቅ ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ስፍራ እየሸሹ መሆኑም ነው የተነገረው።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆን በሚደግፉ ሀይሎች እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይሎች ደጋፊዎች መካከል በሳለፍነው እሁድ ምሽት ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።
ሁለቱም ሀይሎች በሞቃዲሾ ከተማ የተለያዩ ስፍራዎችን የተቆጣጠሩ ሲሆን፤ በተለይም ምሽት ላይ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መኖሩ ተነግሯል።
የመንግስት ደጋፊ ሀይሎች ሙስታቅባል የተባለ የሚዲያ ተቋምን መቆጣጠራቸውን እንዲሁም የተቋሙን መሳሪያ በማውደም ሰራተኞችን መደብደባቸው እየተነገረ ይገኛል።
የሶማሊያ ፓርላማ የፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የስልጣ ዘመንን በሁለት ዓመት ያራዘመ ቢሆንም፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይሎች ግን ውሳኔውን አንቀበልም ብለዋል።
ይህንን ተከትሎም በሀገሪቱ ውጥረት ሰፍኖ የቆየ ሲሆን፤ ባሳለፍነው እሁድም ወደ ግጭት አምርቷል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደ ጎረቤት ሀገር የሶማሊያ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ኢትዮጵያንም ያሳስባል ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን አሁን ያለው ችግር በሞቃዲሾ ከተማ ብቻ መሆኑ እና ሌላው የሀገሪቱ ክፍል የተረጋጋ በመሆኑ ይቆጣጠሩታል በሚል በሚል ተስፋ ማድረጋቸውንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡