የሶማሊያ ምክር ቤት የሃገሪቱን መንግስት ስልጣን ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት አራዘመ
የፋርማጆ መንግስት የስልጣን ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ ሶማሊያ ብዙዎችን ለስጋት በዳረገ ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች
ምክር ቤቱ ከ2 ባልበለጡ ዓመታት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል
የሶማሊያ ተወካዮች የታችኛው ምክር ቤት የቀረበለትን አዲስ የምርጫ ህግ አጸደቀ፡፡
ህጉ የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ከሁለት ባልበለጡ ዓመታት ውስጥ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን እንዲያካሂድ የሚጠይቅ ሲሆን በአብላጫ የድጋፍ ድምጽ ጸድቋል፡፡
በ149 የድጋፍ፣ በ3 የተቃውሞ እና በ1 የተዓቅቦ ድምጽ መጽደቁንም የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ሙሃመድ ሙርሳል አስታውቀዋል፡፡
የአዲሱ የምርጫ ህግ መጽደቅ የፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ (ፋርማጆ)ን የስልጣን ዘመን የሚያራዝም ነው፡፡
መንግስታቸው ምርጫው እስከሚካሄድ ድረስ ቀጣዮቹን ሁለት ዓመታት ስልጣን ላይ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
የፋርማጆ የስልጣን ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ ሶማሊያ ብዙዎችን ለስጋት በዳረገ ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች፡፡
በተለይም የፕሬዝዳንቱ የስልጣን ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ምርጫ እንዲካሄድ ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም ተደርሶ የነበረው ስምምነት አለመተግበሩ ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር፡፡
የፌዴራል መንግስቱ እና ከክልል መንግስታት መሪዎች ጋር የከረረ ቅራኔ ውስጥ እንዲገባም ምክንያት ሆኗል፡፡
ቅራኔው ለመፍታት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ተቋማት ጭምር የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡
ዜጎች ፓርላማው መልሶ የሰጣቸውን የመምረጥ መብት እንዲጠቀሙበት ያሳሰቡት ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ውሳኔውን “ታሪካዊ” ሲሉ አድንቀዋል፡፡
ሆኖም ውሳኔው ምክር ቤቱን በገለልተኛነት ከወቀሱ ተቺዎች አላመለጠም፡፡ “የፕሬዝዳንቱን ስልጣን ለማራዘም የተደረገ ነው” ሲሉም አንዳንዶች ተችተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ተመድ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ኢጋድ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ከተወያዩ በኋላ “ለሶማሊያ ብሄራዊ ጥቅም ቅድሚያ” እንዲሰጥ የጋራ መግለጫ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡