የሶማሊያ ፕሬዝደንትን ስልጣን የማራዘም ውሳኔ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ተቃወሙ
የሶማሊያ ፓርላማ ውሳኔ ተቀይሮ በምርጫው ላይ ስምምነት ካልተደረሰ በሀገሪቱ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአውሮፓ ሕብት ገልጿል
ህብረቱ እና አሜሪካ “የሶማልያ የፖለቲካ ተዋናዮች በምርጫ ዙርያ መክረው ስምምነት ላይ እንዲደርሱ” አሳስበዋል
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ ፣ ምንም እንኳን የስልጣን ዘመናቸው ባለፈው የካቲት 8/2021 ቢያበቃም የሶማሊያ ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት የፕሬዘዳንት ሞሀመድ ፋርማጆን የስልጣን ዘመን በሁለት አመት ማራዘሙን ተቃውመዋል፡፡
ጆሴፕ ቦሬል የሶማሊያ ፓርላማ ውሳኔ በአውሮፓ ህብረትም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ሶማሊያን በስምምነት” እንደገና ለመገንባት ሲደረግ የነበረውን የረዥም ጊዜ ጥረት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡
የአውሮፓ ህብረትም ሆነ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሶማሊያ ፖለቲከኞች መስከረም 17 ከደረሱበት ስምምነት ውጭ ያለ ማንኛውንም ዓይነት ስልጣንን የማራዘም ውሳኔ እንደማይቀበሉ ሲገልፁ መቆያተቸውንም ጆሴፕ ቦሬል ተናግረዋል፡፡
ጆሴፕ ቦሬል የፓርላማው ውሳኔ “ሶማሊያን የሚበታትን፣ የሶማልያኝም ሆነ የጎረቤት ሀገራትኝ መረጋጋት ወደ ኋላ የሚጎትት ከመሆኑ ባለፈ የሶማሊያን ህዝቦች ጥቅም የማያረጋግጥ ነው” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
ስለዚህም የሶማሊያ የፖለቲካ ተዋናዮች በአስቸኳይ ወደ ድርድር ተመልሰው በመስከረም 17 ስምምነት መሰረት ምርጫ በሚያካሂዱበት ሁኔታ ይ መምከር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚገደድ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካዩ ጆሴፕ ቦሬል አስጠንቅቀዋል፡፡
የሶማሊያ ፓርላማ ውሳኔ ከአሜሪካም ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ፣ አሜሪካ ውሳኔውን የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ የማረጋገጥ ሂደትን የሚያደናቅፍ ነው ብላለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሶማሊያ መሪዎች በአስቸኳይ ወደ ጠርጴዛ ተመልሰው እንዲመክሩና ከስምምነት እንዲደርሱም ጥሪ አቅረበዋል፡፡