የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ መሪዎችን እንዲያደራድር ጠየቁ
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበሩ ፌሊክስ ሼስኬዲ የፋርማጆን የ“አደራድሩን ጥሪ” ተቀብለዋል
ሶማሊያ አሁንም ባልተቋጩ ድርድሮችና የምርጫ ውዝግብ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ለሶማሊያ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ ለማበጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ እንደነበሩ ተናግረዋል ፡፡
ፋርማጆ ይህንን ያሉት እሁድ ምሽት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ባደረጉት ያልተጠበቀ ጉብኝት ፤ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲ ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ነው ፡፡
የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ውይይቱን እንደሚያመቻችና የአፍሪካ ህብረትን እንደሚቀበልም ነው ፋርማጆ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራቸው በኩል የገለፁት ፡፡
“ሶማሊያ ሰላማዊ ፣ ሁሉንም አካታች እና ወቅታዊ ምርጫን ለማካሄድ የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ ፤ በሶማሊያ መሪነት እና በሶማሊያ ባለቤትነት የሚሰናዱ ውይይቶችን ለማካሄድ አፍሪካ ህብረት የሚጫወተውን ሚና (የፋርማጆ) መንግስት በደስታ ይቀበላል ብለዋል” ሚኒስቴሩ በትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው ፅሁፉ፡፡
ቀደም ሲል የሼስኬዲ ቢሮ ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በትዊተር የሰፈረው መግለጫ እንዳስታወቀው ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ለሁለት ሰዓታት ከተገናኙ በኋላ ፋርማጆ በሶማሊያ ቀውስ ውስጥ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ድርድርን እንዲያመቻቹና የአፍሪካ ህብረት በፕሬዝዳንትነት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል ፡፡
መግለጫው በሁለቱ መካከል የተደረገው ውይይት በሶማሊያ የፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበርም ነው ያለው፡፡
የኮንጎው ፕሬዝዳንት ሼስኬዲ ፋርማጆ ያደረጉትን ተነሳሽነት በደስታ እንደተቀበሉ ጽህፈት ቤታቸው ገልፀዋል፡፡
በቅርቡ የሶማሊያ የፖለቲካ ተዋናዮች የሶማሊያ ፕሬዝደንትን ስልጣን የማራዘም ውሳኔ ማሳለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የሶማሊያ ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት የፕሬዘዳንት ሞሀመድ ፋርማጆን የስልጣን ዘመን በሁለት አመት ማራዘሙን በአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ተቃወሙ ገጥሞታል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል የሶማሊያ ፓርላማ ውሳኔ በአውሮፓ ህብረትም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ሶማሊያን በስምምነት” እንደገና ለመገንባት ሲደረግ የነበረውን የረዥም ጊዜ ጥረት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ነበር የገለፁት፡፡
የአውሮፓ ህብረትም ሆነ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሶማሊያ ፖለቲከኞች መስከረም 17 ከደረሱበት ስምምነት ውጭ ያለ ማንኛውንም ዓይነት ስልጣንን የማራዘም ውሳኔ እንደማይቀበሉ በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡
ጆሴፕ ቦሬል የፓርላማው ውሳኔ “ሶማሊያን የሚበታትን፣ የሶማልያኝም ሆነ የጎረቤት ሀገራትኝ መረጋጋት ወደ ኋላ የሚጎትት ከመሆኑ ባለፈ የሶማሊያን ህዝቦች ጥቅም የማያረጋግጥ ነው” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የሶማሊያ መሪዎች በምርጫ ዙርያ ከስምምነት የማይደርሱ ከሆነ የአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚገደድ በማስጠንቀቅም ጭምር፡፡
የሶማሊያ ፓርላማ ውሳኔ ከአሜሪካም ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ፣ አሜሪካ ውሳኔውን የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ የማረጋገጥ ሂደትን የሚያደናቅፍ ነው ማለቷ ይተዋሳል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሶማሊያ መሪዎች በአስቸኳይ ወደ ጠርጴዛ ተመልሰው እንዲመክሩና ከስምምነት እንዲደርሱም ጥሪ ማቅረባቸውም እንዲሁ፡፡
በሶማሊያ ያለው ያልተቋጨ ድርድርና ምርጫ ውዝግቡ ሶማሊያን የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡ይህም የቀጠናው አሸባሪው ቡዱን አልሻባብ እድሉን በመጠቀም ዳግም አንሰራርቶ የአፍሪካ ቀንድ የደህንነት ሁኔታን ያዳክማል በሚል በርካቶችን አስግቷል፡፡