ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ቢን ዛይድ ለይፋዊ ጉብኝት ቱርክ ገብተዋል
ፕሬዝዳንቱ ኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን አቀባበል አድርገዋላቸዋል
ሞሃመድ ቢን ዛይድ በቱርክ ቆይታቸው የኤምሬትስና ቱርክን የሁለትዮሽ ትብብር በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ቢን ዛይድ ለይፋዊ ጉብኝት ቱርክ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አቀባበል አድርገዋላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ቢን ዛይድ ፥ ኤርዶሃን በዳግም ምርጫው ካሸነፉና በዓለ ሲመታቸውን ካከናወኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኟቸው የሀገር መሪ ሆነዋል።
ፕሬዝዳንቱ የኤምሬትስ ከፍተኛ ባለስልጣናት ልዑክን እየመሩ ነው ኢስታንቡል የገቡት።
በቱርክ ቆይታቸውም የኤምሬትስ እና ቱርክን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚያሳድጉ ምክክሮችን እንደሚያደርጉ የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚያጎለብቱ ስምምነቶች እንደሚፈራረሙም ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ቢን ዛይድ በህዳር ወር 2021 በቱርክ ጉብኝት ማድረጋቸውና ከፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
በዚህ ወቅትም ኤምሬትስ የቱርክ ኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ለማነቃቃት የ10 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል መግባቷ የሚታወስ ነው።
ኤምሬትስ ቱርክ በርዕደ መሬት አደጋ የከፋ ቀውስ ውስጥ በገባችበት ጊዜም ፈጥና በመድረስ አጋርነቷን አሳይታለች።
ዛሬ ኢስታንቡል የገቡት ሞሃመድ ቢን ዛይድ ከሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር በሚያደርጉት ውይይትም የሀገራቱን ስትራቴጂካዊ ወዳጅነትና ኢኮኖሚያዊ ትብብር በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል።