“ሰነፍ” ዜጎቿን አወዳድራ የምትሸልመው ሞንቴኔግሮ
ከ12 አመት በፊት የተጀመረው ውድድር ለረጅም ቀናት በጀርባ መተኛት ሲሆን፥ አሸናፊው 1 ሺህ ዩሮ ይከፈለዋል

ውድድሩ የሀገሪቱ ዜጎች ሰነፍ ናቸው የሚለውን ብሂል ለመቀልበስ ያለመ ነው ተብሏል
በደቡብ ምስራቅ አውሮፓ የምትገኘው ሞንቴኔግሮ “ሰነፎች”ን የሚያሸልም ውድድር እያካሄደች ነው።
ብሪዜና በተባለው ከተማ የሚካሄደው ውድድር ለረጅም ጊዜ በጀርባ ተንጋሎ መተኛትን ብቻ የሚጠይቅ ነው።
የሞንቴኔግሮ ዜጎች ሰነፎች ናቸው የሚል የተዛባ እሳቤ አለ የሚለው የውድድሩ አዘጋጁ ራዶንጃ ብላጎጀቪች፥ ውድድሩ ይህን አስተሳሰብ ለመቀየር ያለመ ስለመሆኑ ያነሳል።
“አለም በዚህኛው ውድድር ይበልጥ እያወቀን ነው” ሲልም ይገልጻል።
የውድድሩ ህግ መቀመጥንም ሆነ በጀርባ ደገፍ ብሎ ቀና ማለትን አይፈቅድም፤ ወዲያውኑ ከውድድር ያስቀንሳል።
ተወዳዳሪዎች በየስምንት ስአት ልዩነቱ ለመጸዳጃ ከሚሰጣቸው 10 ደቂቃ ውጭ በተዘጋጀላቸው ፍራሽ ላይ ለመተኛት ይገደዳሉ።
ይሁን እንጂ ተኝተው ስልክና ላፕቶፕ መጠቀም እንዲሁም መጽሃፍ ማንበብ ይችላሉ።
ዱብራቭካ አክሲች የተባለች ተወዳዳሪ በ2021 ለ117 ስአት ተንጋላ በመተኛት ሪከርድ ሰብራ ማሸነፏን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
በዚህኛው አመት ውድድር ይህ ክብረወሰን ከ15 ቀናት በፊት ተሰብሯል፤ ከአክሲች የተሻለ “ሰነፍ” ተገኝቷል እንደማለት ነው።
ውድድሩ 20ኛ ቀኑን ይዟል መባሉም የሞንቴኔግሮ ዜጎች የሚነሳባቸውን ወቀሳ ያጠናከረው ይመስላል።
በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው የ23 አመት ወጣት ፍሊፕ ክኔዝቪች፥ የመተኛት ውድድሩን እንደሚያሸንፍ ያምናል። አስቸጋሪው ነገር ከቤተሰብ ለቀናት የመራቁ ጉዳይ ብቻ እንደሆነም በማከል።
በዚህ የ”ሰነፍ ዜጎች” መለያ አዝናኝ ውድድር ሰባት ሰዎች እየተፎካከሩ ሲሆን፥ ለቀናት መተኛት እየከበዳቸው እየወጡ ብቸኛ ሆኖ የሚቀረው አሸናፊ 1 ሺህ ዩሮ ሽልማት ይበረከትለታል ተብሏል።