የዩክሬን 20 በመቶ መሬት በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ይገኛል ተብሏል
ባለፉት አምስት ወራት ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ገለጸ።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 168ኛ ቀኑ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የዩክሬን 20 በመቶ መሬት በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ይገኛል ተብሏል።
ጦርነቱን ተከትሎ ባለፉት አምስት ወራት ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዛሬ ባወጣው መረጃ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ከተጀመረበት የፈረንጆቹ የካቲት 24 ቀን 2022 ጀምሮ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዩክሬናዊያን ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።
በጦርነቱ ምክንያት 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩክሬናዊያን ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ፖላንድ፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ሉቲንያ፣ ቤላሩስ እና ሌሎች ሀገራት መሰደዳቸውን ተመድ አስታውቋል።
ተመድ አክሎም ጦርነቱ አሁንም በመቀጠሉ ምክንያት ተጨማሪ ዩክሬናዊያን እየተሰደዱ መሆኑን ገልጾ፤ ሁለቱ ሀገራትን ጨምሮ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ጦርነቱ ስለሚቆምባቸው መንገዶች እንዲመክሩ አሳስቧል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከሩሲያ ጋር ወደለየለት ጦርነት የገባችው።
168ኛ ቀኑ ላይ በሚገኘው በዚህ ጦርነት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው የዩክሬን ክፍል በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ውሏል። ዩክሬን ከምዕራባዊያን በሚደረግላት የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ ሩሲያን በመመከት ላይ እንደምትገኝ አስታውቃለች።
የዩክሬን ጦር በሩሲያ ጦር እጅ ስር ባለችው ካርኪቭ አቅራቢያ ባደረገው የመልሶ ማጥቃት ዶቭሄንክ የተባለች ከተማን ዳግም መቆጣጠሩን ሮይተርስ ዘግቧል።
በአካባቢው ያለችው ኢዙም እና አካባቢውን ለመቆጣጠር በማጥቃት ላይ የነበረው የሩሲያ ጦር በዩክሬን ጦር በደረሰበት ማጥቃት ማፈግፈጉም ተጠቅሷል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ አማካሪ የሆኑት ኦለክሲ አርሴቶቪች እንዳሉት ካርኪቭ ከተማን ከሩሲያ ለመንጠቅ ከፍተኛ ውጊያ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ፖሊሲ ምክትል ጸሀፊ በበኩላቸው በዩክሬን ምድር እስከ 80 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች እንደተገደሉባት እና እንደቆሰሉባት አክለዋል።
ዩክሬን በሩሲያ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ ከአሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት የጦር መሳሪያ እየተደረገላት ይገኛል።
አሜሪካ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
በአጠቃላይ አሜሪካ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያቆች ለዩክሬን መስጠቷን ዘገባው አክሏል።
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ኔድሜዴቭ በበኩላቸው ሩሲያ በዩክሬን ያሰበችውን እቅድ ማሳካቷ አይቀርም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
aXA6IDMuMTQ1LjQ0LjE3NCA=
ejasoft island