የሩሲያ ጦር በካርኪቭ በኩል ኢዙም የሚባለውን አካባቢ ለመቆጣጠር ቢሞክርም ተምትቶ መመለሱ ተገልጿል
ዩክሬን ወደ ግዛቷ በገባው የሩሲያ ጦር ላይ ድል እየተቀዳጀች መሆኑን ገለጸች፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከሩሲያ ጋር ወደለየለት ጦርነት የገባችው።
168ኛ ቀኑ ላይ በሚገኘው በዚህ ጦርነት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው የዩክሬን ክፍል በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ውሏል።
ዩክሬን ከምዕራባዊያን በሚደረግላት የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ ሩሲያን በመመከት ላይ እንደምትገኝ አስታውቃለች።
የዩክሬን ጦር በሩሲያ ጦር እጅ ስር ባለችው ካርኪቭ አቅራቢያ ባደረገው የመልሶ ማጥቃት ዶቭሄንክ የተባለች ከተማን ዳግም መቆጣጠሩን ሮይተርስ ዘግቧል።
በአካባቢው ያለችው ኢዙም እና አካባቢውን ለመቆጣጠር በማጥቃት ላይ የነበረው የሩሲያ ጦር በዩክሬን ጦር በደረሰበት ማጥቃት ማፈግፈጉም ተጠቅሷል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ አማካሪ የሆኑት ኦለክሲ አርሴቶቪች እንዳሉት ካርኪቭ ከተማን ከሩሲያ ለመንጠቅ ከፍተኛ ውጊያ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ፖሊሲ ምክትል ጸሀፊ በበኩላቸው በዩክሬን ምድር እስከ 80 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች እንደተገደሉባት እና እንደቆሰሉባት አክለዋል።
የሩሲያ መከላከያ በበኩሉ በደበባዊ ዩክሬን የሚገኘው ዛፖሪዝህዚያ የኑክሌር ማዕከልን ባሳለፍነው መጋቢት ላይ የተቆጣጠረችው ቢሆንም የዩክሬን ጦር ይሄንን ማዕከል ሀላፊነት ከሩሲያ ለመረከብ ሀላፊነት በጎደለው መንገድ ተኩስ መክፈቷን አስታውቃለች።
ዩክሬን በሩሲያ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ ከአሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት የጦር መሳሪያ እየተደረገላት ይገኛል።
አሜሪካ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
በአጠቃላይ አሜሪካ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያቆች ለዩክሬን መስጠቷን ዘገባው አክሏል።
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ኔድሜዴቭ በበኩላቸው ሩሲያ በዩክሬን ያሰበችውን እቅድ ማሳካቷ አይቀርም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።