ደቡብ ሱዳን 200 ወታደሮቿ ስልጠና ላይ እያሉ እንደሞቱባት ገለጸች
ወታደሮቹ ሕይወታቸው ያለፈው በልምምድ ወቅት፣ በረሃብ እና በበሽታ እንደሆነ ተገልጿል
ደቡብ ሱዳን ከ22 ሺህ በላይ ወታደሮችን ከሰሞኑ ማስመረቃ ይታወሳል
ደቡብ ሱዳን 200 ወታደሮቿ ስልጠና ላይ እያሉ እንደሞቱባት ገለጸች፡፡
ጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን በትናንትናው ዕለት ከ22 ሺህ በላይ ብሄራዊ ወታደሮች አስመርቃለች፡፡
በዚህ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር (ዶ/ር) ስልጠናው ከባድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
200 ወታደሮችም በስልጠና ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ህመም፣ በረሃብ እና በልምምድ ወቅት ህይወታቸው እንዳለፈ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡
ሰልጣኝ ወታደሮቹ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈው ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ሪክ ማቻር ስልጠናው አጅግ ፈታኝ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን በፈረንጆቹ 2013 ላይ ወደ ከሱዳን ነጻነቷን ባገኘች ከሶስት ዓመት በኋላ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የገባች ሲሆን ከአራት ዓመት በፊት በተደረገ የሰላም ስምምነት ብሄራዊ ጦር እንዲቋቋም ተፋላሚ ወገኖች መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረትም በፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት እና ምክትላቸው ሪክ ማቻር (ዶ/ር) በተናጥል ተሰልፈው ሲዋጉ የነበሩ ታጣቂዎች ወደ አንድ መጥተው የደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ጦር እንዲመሰረት ተአድርገዋል፡፡
የዚህ ስምምነት አካል የሖነው እና 22 ሺህ አባላት ያለው ሰልጣኝ ጦር በትናንትናው ዕለት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የጎረቤት ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮች በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡
በዚህ ስልጠና ወቅት አብዛኞቹ ሟች ሰልጣኝ ወታደሮች በፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እና ሪክ ማቻር የሚመሩ የታጣቂዎች ቡድን አባላት እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
ደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ጦር አሰልጥና ማስመረቋ በሚሊዮን ደቡብ ሱዳናዊያን ሰላ ይመጣል የሚል ተስፋቸውን አንድ እርምጃ እውን እንዲሆን ያደርጋልም ተብሏል፡፡