የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ እንዲቀጥል ወሰነ
ደቡብ ሱዳን፤ በ2018 የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ተጥሎባትም ነበር
የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ኃይሎች የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ነው ማዕቀብ የተጣለባት
በአውሮፓውያኑ 2015 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ የጣለው ማዕቀብ እንዲራዘም መወሰኑን አስታወቀ።
ሀገሪቱ ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ባደረገችው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ነበር ማዕቀብ ተጥሎባት የነበረው። የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ስብሰባ በደቡብ ሱዳን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ባለበት እንዲቀጥል ውሳኔ ማስተላለፉን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት በተጣለባቸው ማዕቀብ ምክንያት ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአባልነት ክፍያቸውን መክፈል አለመቻላቸውም ሲገለጽ ነበር።
ከዚህ ባለፈም ደቡብ ሱዳንና ሌሎች 5 ሀገራት የአባልነት ክፍያ ባለመክፈላቸው ድምጽ እንዳይሰጡ ተመድ ከልክሏቸው እንደነበር ይታወሳል።
የመድ የፀጥታው ምክር ቤት፤ በደቡብ ሱዳን ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ እንዲቀጥል መወሰኑ ከመገለጹ ውጭ ዝርዝር ጉዳዮች አልተጠቀሱም።
በአውሮፓውያኑ 2018 የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ባለመከበሩም፤ ጁባ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ተጥሎባት ነበር።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ደቡብ ሱዳን እና ሌሎች አምስት ሀገራት ከ2019 ጀምሮ የአባልነት ክፍያ ባለመክፈላቸው ድምጽ እንዳይሰጡ መመሪያ ሰጥተው ነበር።
የደቡብ ሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ ዳኦ ማሊክ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባለፈው ዓመት አድርገውት በነበረው ቆይታ ሀገራቸው የተጠየቀችውን 22 ሺህ ዶላር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የላከች ቢሆንም በተጣሉት ማዕቀቦች ምክንያት ገንዘቡ እንደተመለሰ ገልጸው ነበር።
ደቡብ ሱዳን ለአፍሪካ ሕብረት መክፈል ያለባትን ዓመታዊ መዋጮ አለመክፈሏን ተከትሎም መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው አህጉራዊው ተቋም ሀገሪቱን ከሕብረቱ አባልነት አግዷት ነበር።
በኋላ ላይም ጁባ ለአፍሪካ ህብረት መክፈል የነበረባትን የ9 ሚሊየን ዶላር አመታዊ መዋጮ ከፍላ ወደ አዲስ አበባው ተቋም መመለሷ ይታወሳል።