የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት እና የአረብ ሊግ በግጭቱ ዙሪያ ለመምከር አስቸኳይ ስበስባ ጠርተዋል
የእስራኤል መንግስት ለእስራኤል የሰፈራ መርሃ ግብር ግንባታዎች እና ለሌሎች የልማት ተግባራት በሚል ፍልስጤማውያንን በምስራቅ እየሩሳሌም ከመኖሪያቸው ለማስለቀቅ ማቀዱን በመቃወም ፣ ከሰሞኑ በእየሩሳሌም የነበረው ውጥረት እና ግጭት በዛሬው ዕለትም ቀጥሏል፡፡
ዛሬ እስራኤላውያን ወጣቶች ፣ እስራኤል በአውሮፓውያኑ በ1967 በአረብ እስራኤል ጦርነት የእየሩሳሌምን ከተማ ቀደምት የሆነውን ምስራቃዊ ክፍል የተቆጣጠረችበትን ቀን የሚያከብሩበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለት እስራኤላውያኑ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ እና የጀግንነት ዜማዎችን እያዜሙ የፍልስጤማውያን መኖሪያ የሆኑ መንደሮችን ጭምር ያቋርጣሉ፡፡
የእስራኤል ወጣቶችን ተግባር ጸብ አጫሪ እንደሆነ የሚገልጹት ፍልስጤማውያን ለተጨማሪ ተቃውሞ አደባባይ ወጥተው በፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን እንዲሁም ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ መተኮሱን እና ማሰሩን ቀጥለዋል፡፡
ግጭቱ በዋናነት በእየሩሳሌም በሚገኘው የሙስሊሞች ሦስተኛው ቅዱስ ስፍራ በሆነው አል አቅሳ መስጂድ ጊቢ ውስጥ እና በዙሪያው ነው የሚስተዋለው፡፡
የእስራኤል ፖሊሶች ድንጋይ በሚወረውሩባቸው የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የፕላስቲክ ጥይቶችን እና አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ እንዲሁም ውሃ በመጠቀሙ በወሰዱት እርምጃ ከ300 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከነዚህም 228 ሰዎች ወደ ህክምና ማዕከላት ገብተዋል ሮይተርስ እንደዘገበው፡፡ በሌላ በኩል የእስራኤል ፖሊስም በ21 አባላቱ ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡
በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሚሊሻዎች ሶስት ሮኬቶችን እና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን ወደ እስራኤል መተኮሳቸውም ታውቋል። እስራኤል በአጸፋው በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ወደ ሚንቀሳቀሱ የሀማስ ሚሊሻ ታጣቂዎች በታንክ በመታገዝ እርምጃ መውሰዷ ተሰምቷል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ፣ “ሕግ የማስከበር እርምጃችንን በኃላፊነት መውሰዳችንን እንቀጥላለን” ያሉ ሲሆን “በእየሩሳሌም ግንባታ እንዳናከናውን የሚደረጉብንን ጫናዎች አጥብቀን እንቃወማለን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ግጭቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰሞኑን የተከሰተው ግጭት እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል። እስራኤል ፍልስጤማውያንን ከምስራቅ እየሩሳሌም የማፈናቀል ዕቅዷን እንድትተውም ጉቴሬዝ ጠይቀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እና የአረብ ሊግ በግጭቱ ዙሪያ አስቸኳይ ስበስባ መጥራታቸውም ነው የተነገረው።
አሜሪካ፣ ሩሲያ እና የአውሮፓ ህብረትም ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡