ከምስራቅ ወለጋና ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ግጭትን በመሸሽ ከ43 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል- ኢሰመኮ
የሲቪል ሰዎችን ደህንነት ለማስከበር በቂ የፀጥታ ኃይሎች በቋሚነት እንዲሰማሩም አሳስቧል
ጊዳ ኪራሙ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የምስራቅ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስጊ ሁኔታ ይገኛሉም ብሏል
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በመስፋፋት ላይ በመሆናቸውና ባሕሪያቸውን እየቀየሩ ብሔር ተኮር ወደ ሆነ የእርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ የሚችል እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በአካባቢዎቹ ያለውን ችግር ለመፍታት መንግስት በቂ የፀጥታ ኃይሎችን በአፋጣኝና በቋሚነት በአካባቢው ሊያሰማራ እንደሚገባ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ፤ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጊዳ ኪራሙ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የምስራቅ ወለጋ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአስጊ ሁኔታ እንደሚገኙ ገልጾ፣ ወደ ወረዳው የሚወስዱ የተዘጉ መንገዶችን ማስከፈትን ጨምሮ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራሉ ኃይሎች ጋር ሊቀናጁ እንደሚገባ አሳስቦ እንደነበር ገልጿል።
ይሁንና የክልሉ የፀጥታ ኃላፊዎች ለኢሰመኮ እንደገለጹት በኪራሙ ወረዳ፣ ሀሮ ከተማ ላይ የነበረው “የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ለሌላ ስራ አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን” ተከትሎ፣ በሀሮ አዲስ አለም ቀበሌ ከመስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሲቪል ሰዎች “በኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።
በዚሁ ከተማ ይህንኑ ግድያ ምክንያት በማድረግ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት የተደራጁ የተወሰኑ የአካባቢው እና አጎራባች ክልል ነዋሪዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች ቤተሰቦችና ከአካባቢው አስተዳደር አካላት መረዳቱን አስታውቋል።
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በኡሙሩ ወረዳ ደግሞ ከነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች በሆኑና “እራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ” በሚል መሳሪያ እንዲታጠቁ ስለመደረጋቸው ወይም እንደተፈቀደላቸው በሚነገር የአካባቢው ነዋሪዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በተመሳሳይ በርካታ ንጹሃን መገደላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ጥቃቶቹና ግድያዎቹ የብሔር ማንነትን መሰረት አድርገው አንድ ጊዜ በአማራ፤ ሌላ ጊዜ በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በመሆናቸው፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በሆኑ በሁለቱ ብሔር ተወላጆች መካከል ከፍተኛ ውጥረትና የእርስ በእርስ ግጭት ስጋትን እንደፈጠረም ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ግጭቱን በመሸሽ ከምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ፣ ጉደያ ቢላ ወረዳ፣ ኪረሙ ወረዳ፣ ሌቃ ዱለቻ ወረዳ፣ በዲጋ ወረዳ፣ እና ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በአጠቃላይ 43 ሺ 139 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ከዞኑ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት አረጋግጫለሁ ብሏል።
በተጨማሪም ወደ እነዚህ አከባቢዎች የሚያደርሱ መንገዶች አሁንም ዝግ በመሆናቸውና በአከባቢው ያለው ውጥረት አሁንም ባለመርገቡ ምክንያት ሰዎች መሰረታዊ አቅርቦቶችንና ሕክምና ለማግኘት ጭምር በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፤ በተለይም የአካባቢውንም ሆነ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ስምሪት በተመለከተ በተደጋጋሚ እየታየ ያለው አንዱ ችግር የፀጥታ አስከባሪዎች አንድ አካባቢን ለቅቀው መሄዳቸውን ተከትሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ የዚህን ችግር እጅግ አሳሳቢነት ተቋማቸው ከዚህ በፊትም ማሳወቁን አስታውሰው፤ “ግጭቱ ሙሉ በሙሉ ባሕሪውን በመቀየር ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳይለወጥ እንዲሁም የአካባቢው ሰላምና ደህንነት ሙሉ በሙሉ እስከሚረጋገጥ ድረስ በቂ የፀጥታ ኃይሎች በተለይ ለግጭትና ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ በቋሚነት ተመድበው መንግስት የሁሉንም ነዋሪዎች ደኅንነት የማስጠበቅና ከጥቃት መከላከል ግዴታና ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል።
በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስም ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) አሳስበዋል።