“በትግራይ ግጭት ከ 6 ሺህ በላይ ህፃናት ከወላጆቻቸው ተለይተዋል” - ዩኒሴፍ
ዩኒሴፍ በፀጥታ ምክንያቶች 31 የሰብዓዊ እርዳታ ተልእኮዎቹን መፈጸም እንዳልቻለም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል
የዩኒሴፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፣ በትግራይ ከተፈናቀሉት 1.6 ሚሊዮን ሰዎች ከ 720 ሺህ በላይ ሕፃናት ናቸው ብለዋል
የትግራይ ህፃንት ጥበቃ እና ድጋፍ እንደሚሹ የዩኒሴፍ/UNICEF/ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሄንሪታ ፎር አሳሰቡ፡፡
የዩኒሴፍ/UNICEF/ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሄንሪታ ፎር ፣ የትግራይ ክልል ህፃናት ያሉበት ሁኔታን በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ በመግለጫቸው ፣ በትግራይ ግጭት ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሰባት ወራት በህፃናት ላይ እየተፈፀመ ያለው የመብት ጥሰት መጠን የመቀነስ ምልክት የለውም ብለዋል፡፡
ግጭቱን ተከትሎ “ከ 6,000 በላይ ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተዋል” ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፡፡ አሁንም ቢሆን ተደራሽ ባልሆኑ የተለያዩ አከባቢዎች ድጋፍ የሚፈልጉ ብዙ ልጆች ይኖራሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው አስረድቷል፡፡
“ሴቶች እና ልጃገረዶች አሁንም ድረስ ለአስፈሪ የፆታ ጥቃት እየተዳረጉ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፣ “ውጊያው ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ለጥቃት ከተጋለጡት 540 በላይ ሴቶች በዩኒሴፍ እርዳታ አግኝተዋል ፤ ነገር ግን በደህንነት እጦትና የበቀል እርምጃን በመፍራት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተጠቂዎች አስፈላጊውን እንክብካቤና አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ ሆኗል” ሲሉም አክለው ገልጸዋል፡፡
ሄንሪታ ፎር “ልጆች ፣ ወላጆች እና እርዳታ ሰጪዎች በበቀል ስሜት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ናቸው”ም ነው ያሉት፡፡ በየጊዜው ከዩኒሴፍ አጋሮች የሚደርሳቸው ሪፖርት ይህንን የሚያጠናክር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በትግራይ ክልል 1.6 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል የሚሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ከነዚህም ከ 720,000 በላይ ሕፃናት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ መጠለያ ጣብያዎችና የስደተኞች ካምፖች መጨናነቃቸውን እንዲሁም ከንጽህና መጠበቅ፣ ፆታዊ ጥቃት እና ውሃ ወለድ በሽታዎች ጋር በተያያዘ ጉድለቶች እንዳሉም ነው የዩኒሴፍ ዋና ስራ አስፈፃሚ ያነሱት፡፡
ሄንሪታ ፎር “አብዛኛው የትግራይ አካባቢ ለሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ተደራሽ አልሆነም” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡ አክለውም ፣ ከሚያዝያ ወር መጀመሪያ አንስቶ በዩኒሴፍ እና በአጋር ድርጅቶች የተደገፉ በተንቀሳቃሽ ጤና ፣ በምግብ እና የውሃ አቅርቦት ላይ የሚሰሩ ቢያንስ 31 ተልዕኮዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት መተላለፊያ እንዳያገኙ ተደርገዋል” ብለዋል፡፡
የዩኒሴፍ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ይህን ይበሉ እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በሰጠው መግለጫ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጪ ተቋማት እና ግለሰቦች በትግራይ ክልል እርዳታ ለማዳረስ የማያስችላቸው ምንም አይነት ችግር እንደሌለ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ መንግስት የሰብዓዊ ድርጅቶች ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀዱንም አስታውቋል፡፡ ይሁንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ትግራይ ለመግባት ሲወተውቱት የነበረውን ያክል የሚፈለገውን የእርዳታ መጠን እየሰጡ ባለመሆናቸው ያለውን ቅሬታም ነው መንግስት የገለጸው፡፡