ማዳበርያ እና ምርጥ ዘር ማከፋፈል መጀመሩን የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ
ሰብአዊነት የሚሰማው ሁሉ ለትግራይ እጁ እንዲዘረጋም ኃላፊው ጠይቀዋል
ግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ 222 ሺ ኩንታል ማዳበርያ ተረክበናል ብለዋል
በትግራይ ክልል የማዳበርያና ምርጥ ዘር ማከፋፈል ተግባራት መጀመራቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አባዲ ግርማይ ገለፁ፡፡
ዶ/ር አባዲ በክልሉ 800 ሺ ኩንታል ማዳበርያ ለማስገባት መታቀዱን ገለጸው እስካሁን 222 ሺ ኩንታል ማዳበርያ ከእጃችን ገብቷል ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ምርጥ ዘርን በተመለከተ ከለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ለማሰባበስብ እቅድ ተይዞ ነበር ያሉት ኃላፊው የዘገየ ቢሆንም ከታቀደው 97 ሺ ኩንታል 38 ሺ ኩንታል ወደ ትግራይ ክልል መግባቱንም አክለዋል፤ እስካሁን 70 በመቶ የሚሆነው ማዳበርያና ምርጥ ዘር ወደ አርሶ አደሩ ለማዳረስ መቻሉን በመጠቆም፡፡
የቢሮ ኃላፊው የግብርና ግብአቶችን ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም “የትራንስፖርት ችግር” ፈተና ሆኗልም ብለዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ለኢቢሲ ትግርኛ በሰጡት የስልክ መረጃ “በዚህ ሳምንት ትራንስፖርት አግኝተናል፤ ዘር የምናጓጉዝ ይሆናል፤ ግን አሁንም ቢሆን የትራንስፖርት ችግር እጅግ ፈታኝ ነው”ም ነው ያሉት፡፡
በስልክ ቆይታቸው “የማረስ ችግር ሁለተኛው ፈተና ነው” ያሉት ዶ/ር አባዲ፤ በሚፈለገው ልክ ለማረስ ባይቻልም አርሶ አደሩ ባለው ለማረስ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ቢሮ ኃላፊው ከአሁን ቀደም ለአል-ዐይን አማርኛ በሰጡት መረጃ “ቤት ንብረቱ ተዘርፏል” ያሉለት የትግራይ ህዝብ የእርሻ በሬዎች እንደሌሉት መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡