ከዓለማችን አምስት ህጻናት አንዱ በቂ ውሃ እንደማያገኝ ድርጅቱ ገልጿል
የተመድ የዓለም ህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በዛሬው ዕለት የሚከበረውን የዓለም ውሃ ቀንን አስመልክቶ ባጠናው ዓመታዊ ጥናት በዓለማችን ሀገራት ካሉ አምስት ህጻናት መካከል አንዱ (1/5) በቂ ውሃ እያገኘ አይደለም።
በዓለማችን ካለው ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚሆነው በቂ ውሃ የማያገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 450 ሚሊዮኑ ህጻናት እንደሆኑ ጥናቱ ጠቁሟል።
የዩኒሴፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሄነሪታ ፎር እንዳሉት የውሃ እጥረቱ በ80 የዓለማችን ሀገራት ያለ ሲሆን ምስራቅ አፍሪካ እና ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የውሃ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ድርጅቱ በድረገጹ አስታውቋል።
ህጻናት ውሃ ፍለጋ ረጅም መንገድ ይጓዛሉ፤ በውሃ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እየተገለሉ እና ንጽህናቸውን ባለመጠበቃቸው ለተለያዩ ውስብስብ ችግሮች እየተዳረጉ ነውም ብለዋል ዳይሬክተሯ።
እንደ ጥናቱ ከሆነ በምስራቅ እና ደቡባዊ የአፍሪካ ሀገራት ከሚኖሩ ህጻናት መካከል 58 በመቶዎቹ በቂ ዕለታዊ የውሃ አቅርቦት የላቸውም።
ምዕራብ እና ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ደቡብ እሲያ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በአንጻራዊነት የውሃ ችግር ያለባቸው ቀጣናዎች እንደሆኑም ጥናቱ ይጠቁማል።
ከፍተኛ የውሃ ችግር ካለባቸው ሀገራት መካከልም አፍጋኒስታን፣ ቡርኪናፋሶ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ሀይቲ፣ ኬኒያ ፣ፓፕዋ ኒው ጊኒ ፣ ፓኪስታን ፣ ናይጄሪያ ፣ ሱዳን ፣ ታንዛኒያ፣ የመን እና ኒጀር ተጠቅሰዋል።