ከ70 በሚበልጡ የሱዳን እና ዓለም አቀፍ ከተሞች ታላቅ የተቃዉሞ ሰልፍ እተካሄደ ነው
ሰልፎች “ጀነራል አብደልፈታህ አል-ቡርሃን ሶሞኑን የወሰድዋቸው እርምጃዎች” የሚቃወሙ ናቸው ተብለዋል
ሰልፎቹን በማስተባበር የሱዳን አክቲቪስቶች ትልቅ ሚና መጫወታቸው ተገልጿል
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን፣ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ መታሰርና የሽግግር መንግስቱ መፍረስ በመቃወም በሱዳን መዲናዋ ካርቱምን ጨምሮ በመላው ዓለም ታላቅ ሰልፍ በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ካርቱም፣ ሌሎች በሱዳን የሚገኙ 25 ከተሞች እንዲሁም አሜሪካ እና ካናዳን ጨምሮ 45 የአውሮፓ ከተሞች ሱዳናውያን ተቃሟቸውን እያሰሙባቸው ያሉ ከተሞች ናቸው ተብለዋል፡፡
በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ሀገሪቱን በትረ ስልጣን የጨበጡት ሌ/ጀነራል አብደልፋታህ አል-ቡርሃን የሽግግር መንግስቱ ሉዓላዊ ም/ቤት ማፍረሳቸው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት የተወከሉና ድርጊቱን የተቃወሙ አምባሳደሮች ማባረራቸው የሚታወስ ነው፡፡
በዛሬው እለት በመካሄድ ላይ ያለው በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን የተሳተፉበትና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጸጥታ ሃይሎች የተሰማሩበት የተቃውሞ ሰልፍም፤ የአፍሪካ ቀንዷ ሀገረ ሱዳን ዜጎች የጀነራል አል-ቡርሃን እርምጃ እንዳልተቀበሉት የሚያመላክት መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
ሮይተርስ የሀኪሞችን ኮሚቴ ጠቅሶ እንዘደገበው፤ በተቃውሞ ሰልፉ እስካሁን ሁለት ሰዎች ተገድለዋል፡፡
የዛሬው ሰልፍ የሱዳን አክቲቪስቶች በስልክ መልዕክትን በማሰራጨት፣ በመቀስቀስ እና በየጎዳናዎች መፈክሮች በመለጠፍ ያስተባበሩት በትልቅ ህዝባዊ ማዕበል የታጀበው የተቃውሞ ሰልፍ መሆኑ ተስተውለዋል፡፡
“የጀነራል አል-ቡርሃን እርምጃዎች ይቀልበሱ፣ የሲቪል መዋቅሩ ወደ ስልጣን ይመለስ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የተጣለው እገዳ ይነሳ፣ፖለቲከኞች ይፈቱ እና በመንገድ ላይ የፈሰሰው የጸጥታው ሃይል ገለል ይበልልን” ሰልፈኞች እያንጸባረቅዋቸው ካሉ መፈክሮች ናቸው፡፡
ሶሞኑን በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የሱዳን ጦር በሽግግር መንግስት ውስጥ የነበረውን የሲቪል ክንፍን ከስልጣን ማስወገዱ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ የጦሩ እርምጃ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን አስቆጥቷል፣ በዚህም ድረጊቱን በመቃወም አዳባባይ ወጡ ሀገሪቱ ዜጎች የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካቶች ህይወታቸው እንዲያጡ እና እንዲቆስሉ ምክንያት ሆኗል፡፡