ሌ/ጄ አል-ቡርሃን በአሜሪካና አውሮፓ ህብረት የሚገኙትን ጨምሮ 6 የሱዳን አምባሳደሮችን ከስራ አባረሩ
የተባረሩት አምባሳደሮች በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት የተቃወሙ ናቸው ተብለዋል
የሱዳን ጦር አዛዥ እርምጃ አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተቃውሞ ገጥሞታል
የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን አሜሪካ እና አውሮፓ ህብርትን ጨምሮ በስድስት ሀገራት የሱዳንን የወከሉ አምባሳደሮችን ከስራ አሰናበቱ።
ከቀናት በፊት በሱዳን የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ፤ በ12 ሀገራት የሚገኙ የሱዳን አምባሳደሮች ድረጊቱን እንደሚቃወሙ ባወጡት የጋራ መግለጫ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
- ጠ/ሚ አብደላ ሀምዶክ አሁንም የሱዳን ሕጋዊ መሪ መሆናቸውን የአውሮፓ ህብረት ገለፀ
- “አብደላ ሀምዶክ እስር ቤት ሳይሆን እኔ ቤት ነው ያለው” ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አልቡርሀን
ድረጊቱን የተቃወሙት የሱዳን አምባሳደሮች በአሜሪካ፣ቻይና፣ፈረንሳይ፣ቤልጅየም፣ አውሮፓ ህብርት፣ ስዊዘርላንድ፣ የተመድ ኤጀንሲዎች፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኳታር፣ ኩዌት፣ ቱርክ፣ ስዊድን እና ካናዳ የሚገኙ ናቸው።
ሌ/ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን በሱዳን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ፤የሉአላዊ ምክር ቤት እና ሚኒስትሮች ምክር ቤት ማፍረሳቸው፣ የክልሎች አሰተዳዳሪዎች እና ሌሎች አመራሮች ከስልጣን ማሰናበታቸው፣ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዓብደላ ሓምዶክን ጨምሮ ሚኒሰትሮች ማሰራቸው፣ በመላ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አቃጅ ማወጃቸው እንዲሁም ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲቋረጡ ማድረጋቸው ይታወቃል።
በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላህ ሃምዶክን ከእስር መለቀቃቸው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትናንትናው እለት በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድረገው ነበር።
ወታደራዊ ምንጮች እንደሚጠቁሙትም ሃመዶክ አሁን ላይ ወደ መኖርያ ቤታቸው መመለሳቸውን ነው።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የስልክ ቆይታ እንዳደረጉ ያስታወቁት ብሊንከን፤ በሃምዶክ መፈታት መደሰታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ አሁንም በእስር ላይ ያሉ ሌሎች የሲቪል አስተዳደር አመራሮች እንዲፈቱ አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በካርቱም የሚገኙ የፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኖርዌይ፣ ብሪታንያ፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምባሳደሮች፤ የተባረሩትን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላህ ሃምዶክን በመኖሪያ ቤታቸው እንደሚያገኟቸው አስታውቋል።
እስካሁን በሱዳን የተመድ መልእክተኛው ገርማን ቮልከር ፐርተስ ሃምዶክን ማግኘታቸውንም ነው ተመድ ያስታወቀው።