የሱዳን የፀጥታ ሀይሎች ተቃውሞ በሚያሰሙ ዜጎች ላይ የሀይል እርምጃ እንዳይወስዱ አሜሪካና ብሪታኒያ አስጠነቀቁ
በሱዳናውያን በሀገሪቱ ጦር የተፈፀመውን መፈንቅለ መንግስት ተቃውመው አደባባይ እየወጡ ነው
የሱዳን ጦር እርምጃን ተከትሎ በተካሄዱ ሰልፎች የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉና ከ140 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል
የሱዳን የፀጥታ ሀይሎች ተቃውሞዋቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማሰማት አደባባይ በሚወጡ ዜጎች ላይ የሀይል እርምጃ እንዳይወስዱ አሜሪካና ብሪታኒያ አስጠንቅቀዋል።
በዛሬው እለት የሱዳን ጦር በሲቪል አስተዳደሩ ላይ የወሰደውን እርምጃ በመቃወም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሲዳናውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሞዋችን እንደሚያሰሙ ይጠበቃል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ የሱዳን የፀጥታ ሐይሎች ዛሬ ቅዳሜ ሱዳናውያን ለማድረግ ባሰቡት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሰብአዊ መብት ሊያከብሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንዲሁም የፀጥታ ሀይሎች ተቃውሞዋቸውን በሰላማዊ መንገድ በሚያሰሙ ሰዎች ላይ የሀይል እመርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል።
የሱዳን ህዝቦች ዴሞክራሲን ለማስፈን በሚያደርጉት ሰላማዊ ትግል አሜሪካ ከጎናቸው መሆኗንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው ባስተላፉት መልእክት አስታውቀዋል።
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ እና ልማት ቢሮም በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መልእክት፤ የሱዳን የፀጥታ ሀይሎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞዋቸውን የሚያሰሙ ዜጎችን መብት ሊያከብሩ ይገባል ብሏል።
“በርካታ ሱዳናውያን ዛሬ ለተቃውሞ አደባባይ ይወጣሉ” ያለው ቢሮው፤ “የፀጥታ ሀይሎች በዚሁ ወቅት የዜጎችን ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሊያከብሩ ይገባል” ሲል አሳስቧል።
ባሳለፍነው ሰኞ ሱዳን ጦር ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና የካቢኔ አባሎች በማስር ስልጣኑን መቆጣጠራው ይታወሳል።
በጦሩ እርምጃ የተናደዱት በርካታ ሱዳናውያን ወደ ካርቱም አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ማሰማት የጀመሩ ሲሆን፤የተቃውሞ ሰልፎቹን ወደ አመፅ መለወጣቸውን ተከትሎ የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን ከ140 ሰዎች በላይ መቁሰላቸውም ይታወሳል።