በተከበበችው የሱዳኗ አልፋሸር ከ 700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተመድ አስታወቀ
የተመድ የመብት ቢሮ እንደገለጸው ከባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በአልፋሽር ቢያንስ 782 የሞቱ እና 1143 የተጎዱ ሰዎችን መዝግቧል
በዳርፉር የመጨረሻ ይዞታውን ይዞ ለመቆት ጥረት በሚያደርገው የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የሚደረገው የአልፋሽር ውጊያ እጅግ በጣም ጠንካራ የሚባል ነው
በተከበበችው የሱዳኗ አልፋሸር ከ 700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተመድ አስታወቀ።
በሱዳኗ አልፋሽር ከተማ ከባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ከ 700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስት ድርጅት(ተመድ) የሰብአዊ መብት ኃላፊ በዛሬው እለት ተናግረዋል።
ከበባው እና "የማያባራው ውጊያ ህይወትን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ነው" ያሉት የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በከተማዋ ላይ የጣለውን ከበባ እንዲያነሳ ለምነዋል።
"ይህ አሳሳቢ ሁኔታ መቀጠል የለበትም። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከበባውን ማንሳት አለበት።"
የተመድ የመብት ቢሮ እንደገለጸው ከባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በአልፋሽር ቢያንስ 782 የሞቱ እና 1143 የተጎዱ ሰዎችን መዝግቧል።
ጉዳቱ የደረሰው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለበት የመኖሪያ ሰፈር ላይ በሚያደርሰው የማያቋርጥ ድብደባ እና የሱዳን ጦር በሚያደርገው ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ነው ነው ብሏል ቢሮው።
በንጹሃን ላይ የሚፈጸም እንዲህ አይነት ጥቃት ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከል መሆኑን ቢሮው ገልጿል። ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች በንጹሃን ላይ ጥቃት አለመፈጸማቸውን በተደጋጋሚ ያስተባብላሉ፤ በአልፋሽር እና በአካባቢው ጥቃት በመፈጸም እርስበርሳቸው ይካሰሳሉ።
የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል እየተካሄ ያለው ጦርነት 18 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን 12 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን የተመድ ኤጀንሲዎች መረጃ ያመለክታል።
በዳርፉር የመጨረሻ ይዞታውን ይዞ ለመቆት ጥረት በሚያደርገው የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የሚደረገው የአልፋሽር ውጊያ እጅግ በጣም ጠንካራ የሚባል ነው። ሁኔታውን የሚከታተሉ እንደሚሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር የሚያሸንፉ ከሆነ ባለፈው አመት ምዕራብ ዳርፉር እንደሆነው የጎሳ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።