በኦላይን ይሰጣል የተባለው ብሔራዊ ፈተናው በወረቀት በመሰጠት ላይ ይገኛል
ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባው የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከዛሬ ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ እየተሰጠ መሆኑን አል ዐይን አማርኛ ከትምህርት ሚኒስቴር ሰምቷል።
ለፈተናው መሳካት ሲባልም ከየካቲት 21 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የመፈተኛ ቁሳቁሶች የተሰራጩ ሲሆን ተገቢው የጸጥታ ስራ መከናወኑም ተገልጿል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተራዝሞ የቆየው የ2012 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና ከዛሬ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ መገለፁ የሚታወስ ነው።
ሚኒስቴሩ ፈተናውን በኦንላይን ለመስጠት አቅዶ የነበረ ቢሆንም የመፈተኛ ታብሌት ኮምፒውተሮች ግዢ በወቅቱ ሊፈጸም እና ታብሌቶቹ ወደ ሃገር ውስጥ በጊዜው ለመግባት ባለመቻላቸው ፈተናውን በወረቀት ለመስጠት መወሰኑ ይታወቃል።
የትግራይ ክልል ተፈታኞች በክልሉ የሚገኙት የትምህርት መሰረተ ልማቶች በጦርነቱ ምክንያት መውደማቸውን ተከትሎ ፈተናውን በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ነው የሚወስዱት በሚል ሚኒስቴሩ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡
የሚኒስቴሩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ተፈታኞቹ በመቀሌ፣ በአክሱም፣ በአዲግራት እና በራያ የኒቨርስቲዎች ነው የሚፈተኑት፡፡
በክልሉ ከ12ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች እንደሚገኙም የሚኒስቴሩ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡